የዝናቡ መጠንና ሥርጭት አጥጋቢ በሆነባቸው በደቡብና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ፓፓያ በዝናብ ብቻ ሊመረት ይችላል፡፡ የዝናቡ መጠንና ሥርጭት አስተማማኝ ባልሆነበትና ለመስኖ የሚያገለግል ውሃ ባለበት አካባቢ ደግሞ በመስኖ በመ፺ገዝ ፓፓያ ይመረታል፡፡ የመስኖ ውሃ ያለበትና የአየር እርጥበት አነስተኛ የሆነበት ቦታ ለፓፓያ ማምረቻነት ይመረጣል፡፡
ፓፓያ ዓመቱን ሙሉ የተመጣጠነ ውሃ ይፈልጋል፡፡ የውሃ መጠኑና ድግግሞሹ በአፈሩ ተፈጥሮ፣ በተክሉ የዕድገት ደረጃና በማምረቻው ቦታ የአየር ንብረት ይወሰናል፡፡ የውሃ መብዛት የውሃ ማነስን ያህል ወይም የበለጠ ጉዳት ስለሚያስከትል አስፈላጊውን መጠንና ድግግሞሽ ለማወቅ ባለሙያ ማማከር ይጠቅማል፡፡ በአጠቃላይ ተክሉ እንደተተከለ የውሃውን መጠን በማሳነስ ድግግሞሹን መጨመር ሲገባ ተክሉ እያደገ ሲመጣ ደግሞ ድግግሞሹን በመቀነስ መጠኑን መጨመር አስፈላጊ ነው፡፡