መግቢያ


በኢትዮጵያ በደጋማው አካባቢ ከሚመረቱት ዋና ዋና የቅባት እህሎች መካከል ተልባ ከኑግ ቀጥሎ በሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡ የሰብሉ ዋና ጠቀሜታ ገቢ ማስገኘት ቢሆንም ለምግብነትም የማይናቅ አስተዋፅዖ ያበረክታል፡፡ የምግብ ዘይቱ እንደአካባቢው፣ ዝርያው፣ የአመራረትና የምግብ ትንተና ዘዴዎች የሚለያዩ ቢሆንም በአማካይ 40 በመቶ ቅባት፣ 28 በመቶ ካርቦሀይድሬት፣ 21 በመቶ ፕሮቲን፣ 7.6 በመቶ ውሃና 3.4 በመቶ የተለያዩ ማዕድናት እንዳለው የምርምር ውጤቶች ያመለክታሉ፡፡

ተልባ ከሌሎች ሰብሎች በተለየ መልኩ ከፍተኛ ሊኖሌኒክ አሲድ፣ ፌኖሊክ፣ ሊግናንና ፍላቮኖይድ የተሰኙ የእፅዋት ንጥረ- ኬሚካሎችን ስለያዘ ለሰው ጤንነት እጅግ ጠቃሚ ሆኖ ተገኝቶአል፡፡ የቅባት ይዘቱም 57 በመቶ ሊኖሌኒክ፣ 18 በመቶ ሊኖሌይክ፣ 16 በመቶ ኦሌይክ፣ 9 በመቶ እስቴሪክና ፓልማትክ አሲድ ነው፡፡ በተጨማሪም ለተለያዩ አግሮ ኢንዱስትሪዎች፣ ለእንስሳት መኖነትና ለሌሎችም ግልጋሎቶች ስለሚውል በገበያ ላይ ተፈላጊነቱ በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ መጥታል፡፡ ይህንን ከፍተኛ ፍላጎት ለማሟላትና አምራች ገበሬዎች በደንብ እንዲጠቀሙ ለማድረግ ዘመናዊ የአመራረት መመሪያ ማዘጋጀት ያስፈልጋል፡፡