መግቢያ


በኢትዮጵያ ሁለት የጎመን ዘር ዓይነቶች በዋናነት ለዘር ዘይታቸው ይመረታሉ፡፡ እነሱም የአበሻ ጎመንዘር  ( Ethiopian mustard ) እና የአርጀንቲና ጎመንዘር ( Rapeseed) ናቸው፡፡  ሁለቱም የጎመንዘር ዓይነቶች የተቀራረበ የዘር ግንኙነት ስላላቸው ስነ-ፍጥረታቸውና አመራረታቸው በጣም የተቀራረበ ነው፡፡ የአበሻ ጎመንዘር በመካከለኛ፣ የደቡብ፣ የሰሜን እና የደቡብ ምሥራቅ የኢትዮጵያ ደጋማ ቦታዎች ከጥንት ጀምሮ የሚመረት ሰብል ሲሆን፣ ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ እንደተገኘ ይታመናል፡፡ የአርጀንቲና ጎመንዘር አርሲና ባሌ ውስጥ በነበሩ ሰፋፊ እርሻዎች ይመረት የነበረ ቢሆንም በሥር አበስባሽ በሽታ በመጠቃቱ በአሁኑ ወቅት ለምርምር ተግባር ካልሆነ በቀር መዘራቱ የቀረ ሲሆን፣ ወደ ኢትዮጵያም ከ30 ዓመት በፊት እንደገባ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

በኢትዮጵያ ሁኔታ የአበሻ ጎመንዘር ከአርጀንቲና ጎመንዘር የበለጠ ምርታማ፣ የተሻለ በሽታና ድርቅን የመቋቋም እና ሌሎች ለማምረት ተስማሚ የሚያደርገው ባህሪያት ቢኖሩትም፣ የዘይት (40 በመቶ ገደማ ኢሩሲክ አሲድ ስላለው) እና የፋጉሎው (70-160 ማይክሮ ሞል ግሉኮሳይኖሌት ሰላለው) ጥራቱ ከኑግ ጋር ሲነፃፀር አናሳ ነው፡፡ በመሆኑም ለዘይት ተብሎ በስፋት የሚመረተው በኢትዮጵያ ብቻ ነው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በሽታና ድርቅን በመቋቋም ችሎታው የተነሣ በርካታ አገሮች ሰብሉን የማምረት አዝማሚያ ያሳዩና የሙከራ ምርት የጀመሩ መሆናቸው ታውቋል፡፡ የተጠቀሱትን የዘይትና የፋጉሎ ጥራቱም በምርምር ለማሻሻል ጥረት እየተደረገ ነው፡፡

የአበሻ ጎመንዘር ምርታማነት በኢትዮጵያ ከሚመረቱት ሌሎች የቅባት እህሎች ሁሉ ከፍተኛ ነው፡፡ ነገር ግን በዘይትና ፋጉሎ ጥራቱ አናሳነት ዓመታዊ የምርት መጠኑ አነስተኛ ቢሆንም ከጊዜ ወደ ጊዜ ግን እየጨመረ መምጣቱን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ የማዕከላዊ ስታትስቲክስ መረጃ (ባለፉት አምስት ዓመታት) የጎመንዘር ምርት በኢትዮጵያ ከሀያ ዓመት በፊት ካለው ጋር ሲወዳደር ከ1000 በመቶ በላይ ማደጉን ያሳያል፡፡