መግቢያ


ጉሎ ወይም ጫቅማ አገር በቀል የቅባት እህል ነው፡፡ ይህ ተክል በወንዞች፣ በሸጦችና በአጥር አካባቢ በብዛት በወፍ ዘራሽነት በቅሎ ይታያል፡፡ ጉሎ በቁመት፣ በፍሬ ቀለምና መጠን፣ በቅጠል ግንድ ቀለምና ውፍረት፣ በቅርንጫፍ ብዛት፣ በቅጠል መጠን፣ ወዘተ ከፍተኛ የጀኔቲክ ልዩነት ይታይበታል፡፡ ፍሬው ቀይ፣ ጥቁር ወይም ዝንጉርጉር ሲሆን የ1000 ፍሬዎች ክብደት ከ100 ግራም  እስከ 1 ኪሎ ግራም ሊደርስ ይችላል፡፡ የዘይት ይዘቱ ደግሞ እስከ 60 በመቶ ይደርሳል፡፡

ጉሎ ከአጭርና ዓመታዊ እስከ ትንሽ ዛፍና ሰንባች ሊሆን ይችላል፡፡ ሆኖም በመረጣና ማዳቀል አጫጭር፣ ፈጥነው የሚደርሱና ከፍተኛ ምርት የሚሰጡ ዝርያዎች ማግኘት ይቻላል፡፡ ዛላው   ከላይ  ሴቴ ከታች ወንዴ አበባዎች ስላሉትና አልፎ አልፎም በተፈጥሮ ሴቴ ወይም ወንዴ አበባ ብቻ ያላቸው ስለሚኖሩ እነዚህን በመለየትና ከአጫጭር ቁመት ጋር በማዋሀድ የጉሎን ምርት በእጅጉ የሚጨመር ዲቃላ ዝርያ መምረጥ ተችሏል፡፡

የጉሎ ተክል ስሩ እስከ 3 ሜትር ስለሚያድግ እርጥበት ከስር ጀምሮ ያገኛል፡፡ ስለዚህ ከሌሎች  ሰብሎች የበለጠ ድርቅን የመቋቋም  ባህርይ  አለው፡፡  የአገዳ  ሰብሎችን  በሚያጠቁ  በሽታዎች ስለማይጠቃ፤ ለአገዳና ጥራጥሬዎች  በተለይም ለማሽላ ፣ በቆሎ፣ ቦሎቄና ለአኩሪ አተር ተስማሚ የፈረቃ ሰብል ነው፡፡