መግቢያ


ኑግ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገኘው በኢትዮጵያ መሆኑን ብዙዎቹ ዘገባዎች ያረጋግጣሉ፡፡ ታሪካዊ አመጣጡም ዛሬ መጭ ከሚባለዉ የአረም ዝርያ ከብዙ ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ ገበሬዎች በመረጣ የተገኘ ሰብል መሆኑን ተመልክቷል፡፡ ኢትዮጵያ የኑግ ብዝሃ-ዘር ( Germplasm ) ምንጭ ከመሆኗም ባሻገር ከየትኛውም አገር በበለጠ የኑግ ህብለ-ብሄር ክምችት ሀብት ( genetic divesity) እንዳላት ይገመታል፡፡ በ1994 ዓ/ም በተገኘው በማዕከላዊ ስታትስቲክስ ባለስልጣን መረጃ መሠረት ከአጠቃላይ የቅባት ሰብሎች ኑግ ወደ 232,000 ሄክታር የመሬት ሽፋንና ወደ 842,000 ኩንታል የምርት መጠን ድርሻ አለው፡፡ ኑግ በኢትዮጵያ ለረዥም ጊዜ የተመረተ ሰብል ቢሆንም በሀገሪቱ አማካይ ምርታማነቱ 3.4 ኩንታል በሄክታር ብቻ ነው፡፡ የኑግ ዘይት በጥራቱና ለምግብ ማብሰያነቱ ተመራጪነት ያለው ቢሆንም በምርቱ አናሳነት የተፈለገውን ያህል ተመርቶ ለዘይት አምራች ኢንዱስትሪዎች እና ለውጭ ገበያ ማቅርብ አልተቻለም፡፡