ምርት መሰብሰብና ማከማቸት


የቲማቲም ሰብል ከፍተኛ ክትትል ይጠይቃል፡፡ ፍሬው በፀሐይ፣ በወፍ፣ በበሽታና በተባይ ወይም በወቅቱ ባለመሰብሰብ የተነሣ የምርቱ መጠንም ሆነ የጥራት ደረጃው ሊቀንስ ይችላል፡፡ የቲማቲም ፍሬ ገና ቀለሙን መለወጥ ሲጀምር ከተሰበሰበ በአብዛኛው ከላይ በተጠቀሱት የጉዳት መንስኤዎች ሊበላሽ የሚችለውን ምርት ማዳን ይቻላል፡፡

ቲማቲም ማሳ ላይ ከተተከለ ከ75 – 100 ቀናት ውስጥ ምርቱን መሰብሰብ ያስፈልጋል፡፡ እንደዝርያው ዓይነት የምርት መሰብሰቢያው ጊዜ ከ15 እስከ 35 ቀናት ሊቆይ ይችላል፡፡እስከ ዘጠና በመቶ ውሃ-አዘል ሰብል ስለሆነ በምርት አሰባሰቡ፣ ማጓጓዝና ማከማቸት በኩል ከፍተኛ ጥንቃቄን ይጠይቃል፡፡ በየደረጃው አስፈላጊው እንክብካቤ ከተደረገ በሄክታር ከፍተኛ የተጣራ ገቢ ማግኘት ይቻላል፡፡ ቲማቲም ከምርት በኋላ ሳይበላሽ የመቆየት ዕድሜው በጣም አጭር ነው፡፡ ይህን ለማሻሻል ለገበታ  የሚሆን ቲማቲም ገና መቅላት ሲጀምር መልቀም ይገባል፡፡ ይህም ለማቆየትም ሆነ ለማጓጓዝ ይረዳል፡፡ ለፋብሪካ የሚውለው ደግሞ ሙሉ በሙሉ ቀይ ሲሆን መሰብሰብ ይኖርበታል፡፡

ዘር ማምረት

ጥሩ የቲማቲም ምርት ከያዘ ማሳ ጥሩ ዘር ማግኘት ይቻላል፡፡ ለዚህም የዝርያውን ባሕሪያት ያመለከተ፣ ንጹህና ያልተበላሸ፣ ከበሽታ  ነፃ የሆነ ቲማቲም ከማሳ ላይ መርጦ ዘሩን በጥንቃቄ በመለየት ማጠብና ጥላ ቦታ  ላይ ማድረቅ ያሻል፡፡ ከዚያም ዘሩን በንጹህና በደረቅ ቦታ  በማከማቸት  እንደአስፈላጊነቱ መጠቀም ይቻላል፡፡