ሰብል ጥበቃ


ቲማቲም በተለያዩ በሽታዎች  ይጠቃል፡፡ አብዛኛውን ጊዜ በሽታ  ጎልቶ የሚታየው ዝናብ በብዛት ሲዘንብና የአየሩ እርጥበት ከፍ ሲል ነው፡፡ በሽታ እንዳይከሰት ለመከላከል ማሳውን ማጽዳትና ሰብል ማፈራረቅ ተገቢ ነው፡፡ በሽታ ከተከሰተ ደግሞ ለዚሁ አገልግሎት የታወቁትን መድሐኒቶች በወቅቱ መጠቀም ተገቢ ነው፡፡ ዋና ዋና የቅጠል በሽታዎችን እንዲቋቋም ሪዶሚል የተባለውን መድሐኒት 3.5 ኪሎ ግራም በ 500 ሊትር ውሃ በጥብጦ በአንድ ሄክታር ማሳ ላይ መርጨት ያስፈልጋል፡፡

የቲማቲምን ተክል ከሚያጠቁት ተባዮች ውስጥ ዋናው የአፍሪካ ጓይ ትል መሆኑ ይታወቃል፡፡ ችግሩ በሚከሰትበት ጊዜ ሳይፐርሜትሪን የተባለ ፀረ-ተባይ መድሐኒት 75 ግራም በ500 ሊትር ውሃ በጥብጦ በአንድ ሄክታር የቲማቲም ማሳ ላይ በመርጨት ተባዩ የሚያስከትለውን ጉዳት ማቃለል ይቻላል፡፡

የቲማቲም ማሳ በወቅቱ ካልታረመ ለሰብሉ የሚያገለግሉ ምግብ፣ ውሃና ብርሃን በመሻማት በምርትና ጥራት ላይ ጉዳት ይደርሳል፡፡  ከተተከለ ከ20 እስከ 60 ቀናት ውስጥ ማረም ችግሩን ይቀርፋል፡፡ ኦሮባንኬ  የተባለው ጥገኛ አረም ከፍተኛ ጉዳት ያስከትላል፡፡  ይህ አረም አበባ ከማበቡ በፊት ወዲያውኑ ነቅሎ ማስወገድ ወይም ማቃጠል ያሻል፡፡

የበሽታን፣ የተባይንና የአረምን ችግር ለመቀነስ ከቲማቲም ጋር ተመሳሳይነት የሌላቸውን ሰብሎች አፈራርቆ መትከልና ከምርት በኋላ ቅሪቶችን ሰብስቦ ማስወገድ ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ እንደ አፈሩ ፀባይና እንደአረሙ ብዛት ዋና ዋና አረሞችን ለመቆጣጠርና የውሃ ቦዮችን ለማስተካከል በሰብል ወቅት ከ2 -3 ጊዜ መኮትኮት ጠቃሚ ነው፡፡ ተክሉ ምርት መስጠት ከጀመረ በኋላ ደግሞ አልፎ አልፎ ዋና ዋና አረሞችን በእጅ መንቀልና ማስወገድ ይቻላል፡፡ የቲማቲም ማሳ አንድ ጊዜ ሊኮተኮትና ሁለት ጊዜ በእጅ ቢታረም ከፍተኛ ምርት ማግኘት እንደሚቻል የምርምር መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡