አረም
ከፍተኛ የጤፍ ምርት ለማግኘት ማሳው ከአረም ነፃ መሆን አለበት፡፡ በዚህ መሠረት የጤፍ ማሳ ሰብሉ ከበቀለበት ቀን አንስቶ ቢያንስ አንድ ጊዜ (ከ3-4 ሳምንት በኋላ) በእጅ በማረም ከፍተኛ ምርት ማግኘት ይቻላል፡፡ በሌላ በኩል የጤፍ አረምን በተለያዩ ፀረ-አረም መድኋኒቶች ለመቆጣጠር ይቻላል፡፡ ቅጠለ-ሰፋፊ አረሞችን ለመቆጣጠር ሰብሉ ከአራት እስከ ስድስት ቅጠሎች ሲያወጣ ለአንድ ሄክታር አንድ ሊትር ቱ.ፎር.ዲ መጠቀም ይቻላል፡፡
ተባይ
ጤፍ በተባዮች እምብዛም ጉዳት አይደርስበትም፡፡ ይሁን እንጂ የጤፍ ዝንብ፣ ደገዛ፣ ተምችና ፌንጣ በመስክ ላይ ሊያጠቁት ይችላሉ፡፡ ስለሆነም እነዚህ ተባዮች ጉዳት ከማድረሳቸው በፊት ለመቆጣጠር ተገቢውን ክትትል ማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡ በፀረ-ተባይ መድኋኒቶች መጠቀምም ይቻላል፡፡ ጎተራ ከገባ በኋላ ግን በተባይ አይጠቃም፡፡ ከተጠቀሱት የመስክ ተባዮች መካከል አያሎፐስ ሎንጊኮርኒስ የተባለው የፌንጣ ዝርያ ጤፍን በቡቃያነቱ ስለሚያጠፋው የዘር ወቅትን ወደ ሐምሌ አጋማሽ ማድረግ የጉዳቱን መጠን ይቀንሳል፡፡ ፀረ-ተባይ መድኋኒቶችን መጠቀም ካስፈለገ በአንድ ሄክታር 1.5 ኪግ ካሪባሪል (ሲቨን) 85 በመቶ ረጣቢ ዱቄትን ከጤፍ እብቅ ወይም ፉርሽካ እና ሞላሰስ ጋር ለውሶ በማሳው ላይ መበተን አጥጋቢ ውጤት ይሰጣል፡፡