ሰብል ጥበቃ


አረም

የኑግ ማሳ በተለያዩ ዓመታዊ (Annual )፣ ቋሚ ( Perennial) እና ጥገኛ አረሞች ይጠቃል፡፡ እነዚህን አረሞች ለመከላከል ሰብሉ ከተዘራ ከአንድ ወር በኋላ መታረም ይኖርበታል፡፡ በተለይም ዶደርና ኦሮባንኬ የተባሉ ጥገኛ አረሞች በሰብሉ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ስለሚያደርሱ በማሳ ላይ እንደታዩ ወዲያውኑ እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል፡፡ ዶደር በማሳው ውስጥ ከቆዬ አረሙን ከነሰብሉ ነቅሎ ማቃጠል የግድ ሲሆን ኦሮባንኬ ከሆነ ደግሞ ከማበቡ በፊት በመንቀልና ከማሳው በማስወገድ መቆጣጠር ይቻላል፡፡

በሽታ

ኑግን ከሚያጠቁ በሽታዎች መካከል ቅጠሉን የሚሸነቁረው ሹት ሆል ( Shoot hole ) ፣ ግንዱንና  ቅጠሉን የሚያቃጥለው ብላይት ( Blight ) እና አመዳይ ( powedry mildew )  በዋነኝነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ እነዚህን በሽታዎች ለመከላከል በሽታዎቹን የሚቋቋሙ ዝርያዎች መጠቀም ተመራጭነት ያለው ሲሆን ለሹት ሆል ፖሊራም-ዲኤፍ 1.8 ኪ.ግ በሄክታር፣ ሚስትራል 1 ሊትር በሔክታር እና ቲልት 0.5 ሊትር በሔክታር ደጋግሞ በመርጨት በሽታውን መቀነስ ይቻላል፡፡

ተባይ

ኑግን ከሚያጠቁት ተባዮች ውስጥ አበባውን በመብላት ዘር እንዳያፈራ የሚያደርገው የኑግ ዝንብ፣ ዘሩንና ችግኙን የሚመገቡት ፌንጣ መሰል ነፍሳት እና የወንዴውን ዘር በመመገብ ለዘር እንዳይበቃ የሚያደርገው ጥንዚዛ በዋነኝነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ እነዚህንም ተባዮች ለመቆጣጠር የተባዮቹን ጥቃት የሚቋቋሙ ዝርያዎችን ወይም ተስማሚ  ፀረ-ተባይ ኬሚካሎችን ከባለሙያ ምክር ጋር መጠቀም ያስፈልጋል፡፡