የምግብ ይዘት


ዳጉሳ በአገራችን በተለያዩ መልክ ለምግብነት ይውላል፡፡ ለምሣሌ ከዳጉሳ እንጀራ፤ ገንፎ ወይም ሙቅ ሊዘጋጅ ይችላል፡፡ ሆኖም ግን ዳጉሳ በዋናነት የሚያገለግለው እንደ ጠላና አረቄ ያሉ ባህላዊ መጠጦችን ለማዘጋጀት ነው፡፡ዳጉሳ ብቻውን ከተበላ የሆድ ድርቀት ሊያስከትል ስለሚችል በተቻለ መጠን ከጤፍ ወይም ከማሽላ ጋር መቀላቀሉ ጥሩ ነው፡፡ ዳጉሳ ከጤፍ፣ ከማሽላ፣ ከበቆሎ፣ ከስንዴና ከገብስ የበለጠ ከፍተኛ የብረት፣ የካልሲዬምና የካርቦ ሀይድሬት ይዘት ያለው ሲሆን መጠነኛ የሆነ የፕሮቲንና የፎስፈረስ ይዘትም አለው /ሠንዝጠረዥ 1/

ሰብሉ ለነፍሰጡር ሴቶች፣ ለተጎዱና ለተሰበሩ ሰዎች ጠጋኝ ሆኖ መገኘቱን ከአርሶ አደሮች  ከተገኘው መረጃ ለመረዳት ተችሏል፡፡ በዚሁም ምከንያት በ1994/95 ዓ.ም. የመኸር ወቅት ከስድስት በማይበልጡ ገበሬዎች የተጀመረው የሰርቶ ማሳያ ሥራ መነሻነት በአሁኑ ወቅት ከ2ዐዐዐ በላይ የሚሆኑ የሻሸመኔና የሲራሮ ወረዳ ገበሬዎች  ታደሰ የተባለውን የዳጉሳ ዝርያ በማምረት ላይ ይገኛሉ፡፡