የሰብል ጥበቃ


የአረም መከላከልና ቁጥጥር

በአጠቃላይ ሲታይ አረም ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ላላቸው ሰብሎች የሚያስፈልገውን ምግብ (plant nutrients)፣ የፀሐይ ብርሃንንና (Sunlight) እርጥበትን (Moisture) ስለሚሻማ የሰብሎቹን ምርታማነት በከፍተኛ ደረጃ እንዲቀንስ ያደርጋል፡፡ በቆላማ አካባቢዎች የማንኛውም አረም ዕድገት እጅግ ፈጣን በመሆኑ በወቅቱ ካልታረመ ለስንዴ ሰብል የሚሰጠውን ማዳበሪያና የመስኖ ውሃ በእጅጉ ስለሚሻማ  ከ60-90 ፐርሰንት የምርት መቀነስ ሊያስከትል እንደሚችል ከነበረው ተሞክሮ ለማወቅ ተችሏል፡፡ በቆላማ አካባቢዎች እጅግ በርካታ የሣርና ቅጠላቅጠል አረሞች ይገኛሉ፡፡ እነዚህ አረሞች በስንዴ ሰብል ላይ የከፋ ችግር ከማስከተላቸው በፊት ከሰብሉ ውስጥ በሁለት ዋና ዋና መንገዶች ማስወገድ ያቻላል፡፡

1/ በእጅ ማረም

የስንዴ ሰብል ከ2-3 ጊዜ በሰው ኃይል ሊታረም ይችላል፡፡ የመጀመሪያው የእጅ ዓረም የሚከናወነው ሰብሉ ከተዘራ ከ15-20 ባሉት ቀናት ውስጥ ነው፡፡ የዓረም ሥራ በሚካሄድበት ወቅት ዓረሞቹ እንዳይጎረዱና ሰብሉ እንዳይሰባበር በጥንቃቄ ማረም ያስፈልጋል፡፡ ግንዛቤ ሊወሰድበት የሚገባው ነገር ቢኖር የእጅ ዓረም በሚከናወንበት ወቅት እንዳንዱን የበቀለ ዓረም ከነስሮቹ ተነቅሎ ካልተወገደ የእጅ አረማው ከ3 ጊዜ በላይ ለማረም ከማስገደዱም በላይ ለተጨማሪ ወጭና ድካም ይዳርጋል፡፡ ሁለተኛው የእጅ ዓረም የሚከናወነው ከ35-40 ባሉት ቀናት ውስጥ ሲሆን በተመሳሳይ መልኩ በአንደኛ የእጅ ዓረም ወቅት የተከናወኑ ጥንቃቄዎች መተግበር አለባቸው፡፡ ሦስተኛው የእጅ ዓረም በአብዛኛ ከስንዴ ሰብል ጋር የሚመሳሰሉ የሣር ዓረሞችን ለማስወገድ የሚከናወን ነው፡፡ በመስኖ በሚለማበቸው አከባቢዎች አካባቢው ሞቃታማ ስለሆነ በአረም ወቅት የሰብሉ ስሮች ለፀሐይ ብርሐን ሊጋለጡ ከመቻላቸውም ባሻገር በአፈሩ ውስጥ የነበረው እርጥበት በፍጥነት ስለሚተን እርጥበቱን መተካት አስፈላጊ በመሆኑ የዓረም ሥራው እተከናወነ በአለበት ወቅት ቢቻል ቅድሚያ ለታረመው በዕለቱ የመስኖ ውሃ መስጠት ያስፈልጋል፡፡ 

2/ ፀረዓረም መድሃኒትን መጠቀም

የስንዴ አረሞችን ለመቆጣጠር ሁለት ዓይነት ፀረ-ዓረም መድሃኒቶችን መጠቀም ይቻላል፡፡ እነዚህም ፓላስና ደርቢ ይባላሉ፡፡ ፓላስ የተባለው መድሃኒት የሚጠቅመው የሣርና ሰፋፊ ቀጠል ያላቸውን ዓረሞች ለመቆጣጠር ሲሆን የሚረጭበት ጊዜ አረሞቹ ከ4-5 ቅጠል በሚያወጡበት ወቅት መሆን አለበት፡፡ መድሃኒቱ የዓረሞቹን ዕድገት ስለሚገታ ከርጭቱ በኋላ ስንዴው በፍጥነት አድጎ መሬቱን ስለሚሸፍን አዳዲስ አረሞች የመብቀል ዕድላቸው በእጅጉ ይቀንሳል፡፡ የርጭት ጊዜው የሚዘገይ ከሆነ ግን መድሃኒቱ ዓረሞቹን የመቆጣጠር አቅሙ እየቀነሰ ይመጣል፡፡ ለአንድ ሄክታር 0.5 ሊትር ፓላስ በ200 ሊትር ንፁህ ውሃ ተበጥብጦ በሞተራይዝድ ወይም በናፕሳክ መርጫ መሣሪያዎች መረጨት አለበት፡፡

ደርቢ የተባለው ፀረ-መድሃኒት የሚጠቅመው ሰፋፊ ቅጠል ያላቸው አረሞችን ለመቆጣጠር ሲሆን ከርጭት በኋላ ዓረሞቹ ሙሉ በሙሉ ይደርቃሉ፡፡ የመርጫ ጊዜው ከፓላስ ጋር ተመሳሳይ ሲሆን ለአንድ ሄክታር 100 ሚሊ ሊትር ደርቢ በ200 ሊትር ንፁህ ውሃ ተበጥብጦ በሞተራይዝድ ወይም በናፕሳክ መርጫ መሣሪያዎች መረጨት አለበት፡፡ መድሃኒቶቹ ከተረጩ በኋላ ከ3-4 ባሉት ቀናት ውስጥ ለሰብሉ የመስኖ ውሃ መስጠት ያስፈልጋል፡፡ የመድሃኒት ርጭቱ በሚከናወንበት ወቅት እርጭቱን ለሚያካሂዱ አርሶ አደሮች፣ ከፊል-አርብቶ አደሮች ወይም ጉልበት ሠራተኞች አስፈላጊ ለጥንቃቄ የሚረዱ ቁሳቁሶች (Safety materials) እና የምክር አግልግሎት መሰጠት አለበት፡፡ በተጨማሪ  የልማት ሠራተኞች ሁልጊዜ መድኃኒቱ ከመርጨቱ በፊት በመድኃኒቱ መያዣ እቃ ላይ የተለጠፈውን መግለጫ አንብበው በተግባር  መተግባር ይጠበቅባቸዋል።

በሽታን መከላከል

9.2.1. የስንዴ ግንድ ዋግ

በወይናደጋ አካባቢዎች የግንድና የቅጠል ዋግ ሊከሰት ይችላል፡፡ የስንዴ አገዳ ዋግ በሽታ ያለ አንዳች ችግር በስንዴና ከስንዴ ጋር ተዛማችነት ካላቸው የሳር ዝርያዎች ጋር በእድገታቸውም ሆነ በስነ-ዑደታቸው ጊዜ ውስጥ አብሮ የኖረ ነው፡፡ የስንዴ አገዳ ዋግ በሽታ አምጪው ተህዋስያን (Puccinia graminis f.sp tritici) በስንዴ ተክል አገዳ፣ በቅጠሉ ጠርዝና የዛላ ተሸካሚ አንገት ላይ ሊታይ የሚችል የቀይ ቡኒ ቀለም ያለው ምልክት ያሳያል፡፡ የተፈጠረውም ምልክት በስብሉ ቅጠል ላይ በሁለቱም በኩል (በውስጥና በውጭ) መንጠባጠብ ይጀምራል፡፡ ይህ የስንዴ አገዳ ዋግ በሽታ በተለይ ቀደም ብሎ በሰብሉ እድገት ደረጃ ወቅት በወረርሺኝ መልክ ከጀመረ እስከ 100% የሚደርስ የምርት ጥፋት ሊያስከትል ይችላል፡፡ የስንዴ አገዳ ዋግ በሽታን ለመከላከል ፀረ-ሻጋታ ኬሚካል ቀደም ብሎ በመርጨት ወይም በሽታውን ሊቋቋሙ የሚችሉ ዝርያዎችን መጠቀም አስፈላጊ ነው፡፡ አንድ ዝርያ ይህንን በሽታ የመቋቋም አቅሙን ማጣት ከጀመረ ከፍተኛ የምርት ኪሳራ በአርሶ አደሮች ላይ ከመድረሱ በፊት ዝርያውን ከምርት አስወጥቶ በሌላ በሽታውን ሊቋቋም በሚችል ዝርያ መተካት ተገቢ ነው፡፡

የስንዴ ቅጠል ዋግ

በቅጠል ላይ የሚፈጠረው የስንዴ ዋግ በሽታ ምልክት በግንዱ ላይ ከሚፈጠረው የዋግ በሽታ ጋር በእጅጉ ተመሳሳይ ቢሆንም በቀለሙ ግን ደማቅ ብርቱካናማ ወይም ቡናማ በመሆኑ ምክንያት ቡናማ ዋግ ይባላል፡፡ ሌላኛው የስንዴ ቅጠል ዋግ ከግንድ ዋግ በሽታ ልዩ የሚያደርገው ባህሪ የበሽታ አስተላላፊው ተህዋስያን መራቢያ አካል (ዘር) የሚበተነው ከቅጠሉ የላይኛው ጠርዝ ላይ መሆኑ ነው፡፡ ቀደም ሲል ከተዘረዘሩት ሶስት ዓይነት የስንዴ ቅጠል ዋግ አስተላላፊ ተህዋስያን መካከል Puccinia recondita f. sp. Tritici የተባለው ዝርያ በተለያየና ሰፊ የሆነ የመላመድ ችሎታ ያለው ነው፡፡ በባሕሪውም መካከለኛ የሆነ የሙቀት መጠን ያለበት አካባቢ ስለሚፈልግ በዓለም ዙሪያ የስንዴ ሰብል አምራች የሆኑ አካባቢዎች ሁሉ በስንዴ ቅጠል ዋግ በሽታ ተጠቂ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ይህንን በሽታ ለመከላከል የሚያስችሉ ፀረ-ሻጋታ (fungicides) ኬሚካሎች በቀጣይ የተዘረዘሩ ቢሆንም በሽታውን ሊቋቋሙ የሚችሉ ዝርያዎችን መጠቀም የተሻለ አማራጭ መንገድ ነው፡፡  

የስንዴ ዋግን መቆጣጠር የሚችሉ የተለመዱ የፀረ- ሻጋታ ኬሚካሎችና የአጠቃቀም መጠን

በሞቃታማና ዝቅተኛ ቦታዎች የሙቀቱ መጠን ከፍተኛ በመሆኑና በአየር ውስጥ የሚገኘው እርጠበት (Relative Humidity of the air) ዝቅተኛ በመሆኑ በደጋው አካባቢ የስንዴ ሰብልን የሚያጠቁ የስንዴ በሽታዎች እስከአሁን አልተከሰቱም፡፡ ስለሆነም እስከአሁን ድረስ በስንዴ በሸታ መከላከል ዙሪያ የተሰራ ሥራ የለም፡፡