የተሻሻሉ አሰራር ዘዴዎችና ቴክኖሎጂዎች


የማሳ ዝግጅት

ለስንዴ ሰብል የሚዘጋጀው ማሳ በሚገባ የለሰለሰና የተደላደለ ወይም የተስተካከለ መሆን ይኖርበታል፡፡ ለስንዴ ሰብል ልማት የታሰበው ማሳ በበሬ ወይም በግመል የሚታረስ ከሆነ እንደ አመራረት ዘይቤውና አፈሩ ዓይነት በአማካይ ከ2-3 ጊዜ ሊታረስ ይችላል፡፡ ከዚያም በግመል ወይም በበሬ በሚሳብ የመሬት ማስተካከያ መሣሪያ (Sledge = ኦበሎ) ማሳውን በማስተካከል ሰብሉ የተስተካከለ የውሃ ስርጭት እንዲያገኝ ይረዳል፡፡

በመስኖ ለሚለሙ ወይናደጋ አካባቢዎች የመጀመሪያው እርሻ ሰብሉ እንደተሰበሰበ በአፈሩ ውስጥ ያለው እርጥበት ሙሉ በሙሉ ከማሳው ውስጥ ተሟጦ ከማለቁ በፊት የሚከናወን ሲሆን ሁለተኛውና ሦስተኛው የእርሻ ሥራ የሚተገበረው መሬቱን ለማስተካከያው መሣሪያ ምቹ ለማድረግ ታስቦ ነው፡፡    

በመስኖ ለሚለሙ ቆላማ አካባቢዎች በመስኖ የሚለሙ ቆላማ አካባቢዎች አመቱን ሙሉ የሚፈስ ውሃ ስላለ ቢያንስ በአመት ሁለት ጊዜ ሰብል ይመረታል፡፡ ለምሳሌ በአፋር፣ ኢትዮጵያ-ሶማሌ ክልሎችና ኦሮሚያ ክልል ፈንታሌ ወረዳ ሁለት ዋና ዋና የዘር ወቅቶች አሉ፡፡ አንደኛው ወቅት ሙቀት ወዳድ የሆኑ  (ጥጥ፣ ሰሊጥ፣ ለውዝ፣ ወዘተ) ሰብሎች የሚዘሩበት ወቅት (ከግንቦት እስከ ሰኔ ወር ባሉት ጊዚያት) ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ እንደ ስንዴ የመሳሰሉ ቅዝቃዜ የሚወዱ ሰብሎች የሚዘሩበት ወቅት (ከጥቅምት እስከ ህዳር ወር አጋማሽ ድረስ) ያለው ጊዜ ነው፡፡ ስለሆነም ለስንዴ ሰብል የሚዘጋጀው ማሳ በበሬ ወይም በግመል ከሆነ ቀደም ሲል የተዘራው ሰብል ከተሰበሰበ ከ15 ቀናት በኋላ በመሬቱ ውስጥ ያለው እርጥበት ሲቀንስ የመጀመሪያው እርሻ ይታረሳል፡፡ በመጀመሪያ የታረሰው ማሳ ለ10 ቀናት በፀሐይ ከደረቀ በኋላ ሁለተኛው የእርሻ ሥራ ይከናወናል፡፡  ሦስተኛው የእርሻ ሥራ የሚከናወነው ዘሩ በሚዘራበት ወቅት ይሆናል፡፡ ከዚያም በግመል ወይም በበሬ በሚሳብ የመሬት ማስተካከያ መሣሪያ (Sledge = ኦበሎ) ማሳውን በማስተካከል ሰብሉ የተስተካከለ የውሃ ስርጭት እንዲያገኝ ይረዳል፡፡

የእርሻ ሥራው የሚከናወነው በትራክተር ከሆነ በሞቃት ወቅት የተዘራው ሰብል ከማሳው ላይ ተሰበሰቦ ማሳው ለ15 ቀን በፀሐይ ብርሃን ከደረቀ በኋላ በሞልድ ቦርድ ወይም ገልባጭ ማረሻ መታረስ አለበት፡፡ ከዚያም የታረሰው ማሳ ከ5-10 ባሉት ቀናት ውስጥ በትራክተር በሚጎተት የመከስከሻ መሣሪያ ተከስክሶ በመሬት ማስተካከያ መሣሪያ መስተካከል አለበት፡፡

የስንዴ ዘር ወቅት        

በመስኖ ለሚለሙ ወይናደጋ አካባቢዎችበወይናደጋ አካባቢዎች የሙቀቱ መጠን አነስተኛ በመሆኑ በበጋው ወቅት ስንዴን በመስኖ ማልማት ይቻላል፡፡ ስለሆነም በአካባቢው በቂ የመስኖ ውሃ ካለ አርሶ አደሮች መሬታቸውን አርሰውና ለመስኖ ውሃ ስርጭት እንዲያመች አድርገው በማዘጋጀት ያለምንም ችግር ስንዴን ማምረት ይችላሉ፡፡

በመስኖ የሚለሙ ቆላማ አካባቢዎች፡- በቆላማ አካባቢዎች የስንዴ የዘር ወቅት የሚወሰነው በሙቀት መጠን ነው፡፡ እንደሚታወቀው በምስራቃዊና ሰሜናዊ የሀገራችን አካባቢዎች የሚገኙት ሞቃታማ ዝቅተኛ ቦታዎች አንፃራዊ የቅዝቃዜ ወቅታቸው ከጥቅምት እስከ የካቲት ወር መጨረሻ ያለው ጊዜ ነው፡፡ ስለሆነም ስንዴ በተፈጥሮው ቅዝቃዜ የሚወድ ሰብል በመሆኑ በእነዚህ አካባቢዎች ከጥቅምት  ወር መጀመሪያ ሳምንት ጀምሮ እስከ ህዳር ወር አጋማሽ ድረስ ያለው ጊዜ ትክክለኛው የስንዴ የዘር ወቅት ነው፡፡ ምክንያቱም በእነዚህ ወራት ውስጥ ከላይ በተጠቀሱት አካባቢዎች አማካይ የሙቀት መጠን ከ24-27 ዲግሪ ሰልሽየስ በመሆኑ ከፍተኛ የስንዴ ምርት ማግኘት ይቻላል፡፡ ከዚህ የግዜ ገደብ ውጭ የስንዴ ሰብል የሚዘራ ከሆነ የምርት መጠኑም ሆነ የዘር ጥራቱ በከፍተኛ ደረጃ በሙቀት ሊጎዳ ይችላል፡፡ በተመሳሳይ መልኩ በደቡብና ምዕራባዊ የሀገሪቱ አካባቢዎች ለሚገኙ ቆላማ ቦታዎች የቅዝቃዜው ወቅት የሚጀምርበትን ወቅት በማጥናትና ግምት ውስጥ በማስገባት ስንዴን መዝራት ይቻላል፡፡    

የዘር መጠንና አዘራር 

በመስኖ በሚለሙ ዝቅተኛ ቦታዎችም ሆነ በወይናደጋ አካባቢዎች ስንዴ በመስመር መዘራት አለበት፡፡ ስንዴን በመስመር መዝራት በሄክታር የሚያስፈልገውን የዘር መጠን ከመቀነሱም በላይ የሰው ሰራሽ ማዳበሪያን ከተክሉ ትክክለኛ እርቀት ጠብቆ ለሰብሉ ለመስጠት፣ አረምንና ተባይን ለመቆጣጠር ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል፡፡ በመስመር የሚዘራ ስንዴ ብዙ ቅጥያዎች (Tillers) ስለሚያወጣ ምርታማነቱ በእጅጉ ይጨምራል፡፡

በወይናደጋ አካባቢ በመስመር ለመዝራት የሚያስፈልገው የዘር መጠን በሄክታር ከ80-100 ኪ. ግ.  ሲሆን የዘሩ የብቅለት ደረጃ ከ95 ፐርሰንት በላይ መሆን አለበት፡፡ በመስኖ በሚለሙ ቆላማ ቦታዎች የሚገኘው አፈር ለም በመሆኑና ውሃን ቋጥሮ የመያዝ አቅሙ ከፍተኛ በመሆኑ ከወይናደጋ አካባቢዎች ጋር ሲነጸጸር የመዋለድ አቅሙ (Tillering Capacity) ከፍተኛ ስለሆነ በመስመር ለመዝራት የሚያስፈልገው የዘር መጠን በሄክታር ከ60-70 ኪ. ግ.  ሲሆን የዘሩ የብቅለት ደረጃ ከ95 ፐርሰንት በላይ መሆን አለበት፡፡ ዘሩ ከ3-4 ሳ.ሜ ጥልቀት ውስጥ ተዘርቶ በአፈር መሸፈን አለበት፡፡

በአጠቃላይ በወይናደጋና ቆላ አካባቢዎች የመስኖ ስንዴን መዝራት የሚቻለው መሬቱን በበሬ በሚጎተት ማረሻ 40 ሳንቲሜትር ስፋት ያለው ሪጅ /መደብ/ በማውጣት ሲሆን በሪጁ/በመደቡ/ ግራና ቀኝ በ20 ሳ.ሜ ርቀት ላይ ነው፡፡ በ40 ሳንቲሜትር ስፋት ሪጅ /መደብ/ በሚወጣበት ወቅት የትልሙ (ቦዩ) ስፋት 20 ሳንቲ ሜትር ይሆናል፡፡ ይህም የመስኖ ውሃ በሚሰጥበት ወቅት ያለምንም ችግር በቦዩ ውስጥ ውሃው ስለሚሄድ በመደቡ ግራና ቀኝ የተዘራው የስንዴ ዘር በቂ ወሃ ያገኛል፡፡ ነገር ግን በመስኖ በሚለሙ ሞቃታማ አካባቢዎች ስንዴን በሰፋፊ ማሳዎች ላይ የሚዘራ ከሆነ በሁለት መንገድ መዝራት ይቻላል፡፡ 1ኛ/ መዝሪያ ማሽን ካለ በመጀመሪያ መስመሩን የሚያወጣውን ሪጀር በ60 ሳንቲሜትር በማስተካከል መሰመሩን ማውጣት ያስፈልጋል፡፡ ከዚያም መዝሪያ ማሽኑን በ30 ሳንቲሜትር በማስተካከል የስንዴውን ዘር መዝራት ይቻላል፡፡ 2ኛ/ መዝሪያ ማሽን ከሌለ መሬቱን በትራክተር በሚጎተቱ ተቀጣይ መሣሪያዎች በማረስ፣ በመክስከስና በማስተካከል 100 ኪ.ግ. የስንዴ ዘር በብተና በመዝራት በ60 ሳንቲሜትር ልዩነት ሪጅ (መስመር) ማውጣት ያስፈልጋል፡፡ በመቀጠልም እንደመሬቱ ሁኔታ እየታየ ከ30 – 50 ሜትር እርቀት ላይ ሪጁን (መስመሩን) መቆራረጥ የስፈልጋል፡፡ ይህም ሰብሉ የተስተካከለ የውሃ ስርጭት እንዲያገኝ ይረዳዋል፡፡

ማዳበሪያ አጠቃቀም

ሰው ሰራሽ (Inorganic Fertilizers) ማዳበሪያ አጠቃቀም

በአብዛኛው የሀገራችን አካባቢዎች በስፋት የተለመዱት ሰው ሰራሽ የማዳበሪያ ዓይነቶች ዳፕና ዩሪያ ሲሆኑ በአሁኑ ወቅት በዋናነት ዳፕን ተክቶ የኤን.ፒ.ኤስ ማዳበሪያ ጥቅም ላይ  ሲውል የቅይጥ ማዳበሪዎችና የአፈር ለምነት ጥናት ውጤት መሠረት ያደረገ የማዳበሪያ ምክረ ሀሳብ የሙከራና ጥናት ሥራዎች በሂደት ላይ ናቸው፡፡

የዳፕ ማዳበሪያ በተፈጥሮው በአፈር ውስጥ ለረጅም ጊዜ የመቆየት ባህሪ ስላለው (የፎስፈርስ ንጥረ ነገር በአፈር ውስጥ ስለማይንቀሳቀስ) ከስንዴ ሰብል ጋር አብሮ ይዘራል፡፡ ለስንዴ ስብል የሚሰጠው የዳፕ ማዳበሪያ መጠን እንደየአካባቢው ሁኔታ ይለያያል፡፡ በአጠቃላይ ሲታይ ግን በወይናደጋ የስንዴ ሰብል የሚሰጠው የዳፕ ማዳበሪያ መጠን እንደየአካባቢው ሁኔታ እስከ 100 ከ.ግ. በሄክታር ይደርሳል፡፡ እስከ አሁን ድረስ በቆላማው አካባቢ በመስኖ ለሚለማው ስንዴ የሚያስፈልገው የዳፕ ማዳበሪያ መጠን የማወቅ ጥናት በሂደት ላይ ቢሆንም 50 ኪ. ግ ዳፕ /በሄክታር በዘር ወቅት ለሰብሉ መስጠት ጥሩ ውጤት እንዳለው እስከአሁን ከተገኘው ተሞክሮ ለማወቅ ተችሏል፡፡ የማዳበሪያው አሰጣጥ ከዘሩ 5 ሳ. ሜትር ርቀት ላይ መስመር በማውጣት ከተጨመረ በኋላ በአፈር በመሸፈን ውሃ መስጠት ያስፈልጋል፡፡ ነገር ግን በሰፋፊ ማሳዎች ላይ ስንዴ የሚለማ ከሆነ ዳፕ ማዳበሪያውን አብሮ ከስንዴው ጋር በብተና በመዝራት መደብ (ሪጅ ማውጣት) እና የውሃ መስጫ ቦዮችን በማዘጋጀት የመስኖ ውሃ መስጠት ያስፈልጋል)፡፡

የስንዴ ሰብል ጤናማ ዕድገት ኖሮት ከፍተኛ ምርት መስጠት የሚችለው በቂ የናይትሪጂን ንጥረ-ነገር ሲያገኝ በመሆኑ ስንዴው በሚዋለድበት (Tillering Stage) እና የአበባ የዕድገት ደረጃ (Flowering stage) ወቅት በሚደርስበት ግዜ በቂ መጠን የናይትሮጂን ንጥረ-ነገርን ማግኘት አለበት፡፡ ለስንዴ ሰብል የሚያስፈልገው የናይትሮጂን ማዳበሪያ መጠን ከቦታ ቦታ እንደአፈሩ ዓይነት የሚለያይ ሲሆን በአፋር ክልል የአዋሽ ተፋሰስን ተከትሎ ከመካከለኛው እስከ ታችኛው አዋሽ ድረስ የአፈሩ ዓይነት ተመሳሳይነት ያለው በመሆኑ በሄክታር ከ100 -150 ኪ. ግ. ዩሪያ ማዳበሪያ መስጠት በቂ ነው፡፡ ዩሪያ ማዳበሪያ ለሰብሉ የሚሰጠው በአብዛኛው ሁለት ጊዜ ሲሆን የመጀመሪያው 50-75 ኪ. ግ በሰብሉ ውስጥ የበቀለው ዓረም ከተወገደ በኋላ ስንዴው መዋለድ ሲጀምር ነው፡፡  የናይትሮጂን ማዳበሪያ በቀላሉ በሙቀት ኃይል የሚተን በመሆኑ የስነዴ ሰብሉ ውሃ በሚጠጣበት ዕለት ከቀኑ አሥራ አንድ ሠዓት በኋላ አየሩ ሲቀዘቅዝ በጭቃው ላይ ከሰብሉ 5 ሳ.ሜትር ራቅ ብሎ በመስመር ይደረጋል፡፡ በጭቃው ላይ የተደረገው ዩሪያ በቀላሉ ሟሙቶ አብዛኛ የሰብሉ ስሮች በአሉበት አካባቢ ስለሚከማች ሙሉ በሙሉ የስንዴው ሰብል ይጠቀመዋል፡፡ በተመሳሳይ መልኩ ቀሪው 50-75 ኪ. ግ. ዩሪያ የስንዴው ሰብል ከማበቡ በፊት በእንቡጥ የዕድገት ደረጃ (Booting Stage) ይሰጠዋል፡፡ በብተና ለሚዘራው ስንዴ ዩሪያ ማደበሪያ የሚሰጠው ሰብሉ ውሃ በሚጠጣበት ከላይ በተጠቀሰው ተመሳሳይ ሠዓት በጭቃው ላይ በብተና ይሆናል፡፡  

የተፈጥሮ ማዳበሪያ አጠቃቀም

የተፈጥሮ ማዳበሪያ በሌሎች የሰው ሰራሽ ማዳበሪያዎች የማይተካውን የአፈር ብስባሽ መጠን (Humus) ለመጠበቅ ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ በመሆኑ እንደየአከባቢው ሁኔታ ኮምፖስት በማዘጋጀት በማሳ ውስጥ መጨመርና የሰብል ቅሪትን በማሳ ውስጥ መተው አስፈላጊ ነው፡፡