የአመራረት ቴክኖሎጂዎች


ትክክለኛ የዘር ወቅት ሰብሉን ከተባይና ከበሽታ እንዲሁም  ለድርቅም ሆነ ለዝናብ ከመጋለጥ ያድናል፡፡ ነገር ግን የጉሎ ተክል ሰብሎች በተሻለ ሁኔታ ድርቅን ስለሚቋቋም፤ የዘር ወቅት ምርቱን ብዙም አያጠቃውም፡፡ ቢሆንም አዋሳ ላይ በተደረገው ሙከራ ከሰኔ አንድ እስከ አስራ አምስት ትክክለኛ የዘር ወቅት መሆኑ ተረጋግጧል፡፡ በዚሁ ጥናት መሠረት 75 ሳንቲ ሜትር በተክሎች መካከልና 80 ሳንቲ ሜትር በመስመር መካከል ወይም 17-857 ተክሎች በሄክታር ያስፈልጋሉ፡፡ አተካከሉም ሁለት ፍሬዎች በአንድ ላይ ይተከሉና ከበቀሉ በኋላ የተሻለውን በመተው አንዱ ይነቀላል፡፡

የጉሎ ማሳ ሁለት ጊዜ መታረስና አንድ ጊዜ መከስከስ አለበት፡፡ ከበቀለ በኋላ አራት ቅጠል ሲያወጣ አንድ ጊዜ ቢታረም ይበቃዋል፡፡ ሆኖም እንደ  ሰርዶና ተመሳሳይ አረሞች ከተከሰቱ መኮትኮት ይኖርበታል፡፡ ጐሎ በማዳበሪያ ለውጥ አያመጣም፡፡ ቢሆንም 69 ኪ.ግ. ዳኘ በሄክታር በዘር ወቅት መጨመር ጥሩ ምርት ያስገኛል፡፡ የመስኖ ውሃ መጠቀምም ከግሽበት በስተቀር የሚሰጠው ጥቅም የለም፡፡

የጉሎ ተክል ዋና ግንድና ቅርጫፎች ያሉት ሲሆን እያንዳንዱ ቅርጫፍ ዛላ አለው፡፡ በእያንዳንዱ ቅርንጫፍ ላይ ያሉት ዛላዎች በቅደም ተከተል ስለሚያብቡና ስለሚደርሱ ሁለት ጊዜ መለቀም አለበት፡፡ ሲለቀም በማጭድ እንደ ማሽላ ወይም ዘንጋዳ እየተቆረጠ በጆንያ ወይም በቅርጫት ወደ አውድማ ሊወሰድ ይችላል፡፡ የተቆረጠው ዛላ  ወደ አውድማ ከተወሰደ በኃላ በዱላ ከተቸበቸበ ከቅርፊቱ ይለቃል፡፡ ነገር ግን ምርቱ እየበዛ ሲሄድ ይህ ዘዴ ብዙም አይረዳም፡፡ በጉሎ ላይ  ዋናው ወሳኝ ችግር መፈልፈል ሲሆን ይህም በጉሎ መፈልፈያ መኪና ይቃለላል፡፡ ዘሩ ለመሰብሰብ ሲደርስም ቅጠሉን አያራግፍም ወይም የቁመቱና የስፋቱ እድገት ቢቆምም ቅጠሉ አረንጓዴ ሆኖ  ይቀጥላል፡፡ ስለሆነም በኮምባይነር ለመሰብሰብ አስቸጋሪ ነው፡፡ በአደጉት አገሮች ጠረ አረም በመርጨት ቅጠሉ ከተራገፈ በኋላ በቀላሉ ይሰበሰባል፡፡ ይህም ሰፊ ማሳ ላይ የተዘራን ሰብል ለመሰብሰብ አመቺ ነው፡፡