የአመራረት ዘዴዎች


የማሳ ዝግጅት

የተልባ ዘሮች ትናንሽ ስለሆኑና ሲበቅሉም ችግኞቹ ትናንሽና ደካማ ስለሚሆኑ በሚገባ የታረሰና የለሰለሰ ማሳ ያስፈልጋቸዋል፡፡ ማሳው ከአረም የፀዳ መሆን አለበት፡፡ ለጥሩ ምርት ማሳው ከ2-3 ጊዜ መታረስና መለስለስ አለበት፡፡

የዘር ወቅት

ከሰኔ አጋማሽ እስከ ሐምሌ መጀመሪያዎቹ አካባቢ ቢዘራ በቀይም ሆነ በጥቁር አፈር ላይ ጥሩ ምርት ይሰጣል፡፡ ሆኖም ቀደም ብሎ መዝራቱ ለድርቅ፣ ለውርጭና ለበሽታ እንዳይጋለጥ ይረዳዋል፡፡

የዘር መጠን

ተልባ አብዛኛውን ጊዜ የሚዘራው በብተና ሲሆን  ውጤቱም አጥጋቢ ነዉ፡፡ ሆኖም በመስመር ሲዘራ በመስመሮቹ መካከል 20 ሤ.ሜ ርቀት ቢኖር የተሻለ ምርት ይሰጣል፡፡ በብተና ሲዘራ ከ30-40 ኪ.ግ በሄክታር በመስመር ደግም 25 ኪ.ግ በሄክታር ዘር በቂ ነዉ፡፡

የማዳበሪያ መጠን

ተልባ በአብዛኛው ያለማዳበሪያ የሚዘራ ቢሆንም 50 ኪሎ ግራም ዳፕና 30 ኪሎ ግራም ዩሪያ በሄክታር ያስፈልጋል፡፡

ሰብል ጥበቃ

አረም

ተልባ  በቡቃያነቱ በቀላሉ በአረም ይጠቃል፡፡ ቢያንስ ሁለት ጊዜ (ተዘርቶ በ3ኛዉ ሳምንትና ከማበቡ በፊት) በማረም የአረም ጉዳትን መቀነስ ይቻላል፡፡ ተልባን ከሚያጠቁት የአረም ዓይነቶችም ዋናው ዶደር (ኩስኩስታ) የተሰኘው ጥገኛ አረም ነው፡፡ አረሙ ሲከሰት ነቅሎ በማቃጠል ወይም በመቅበር ማጥፋት እንዳይከሰት ደግሞ ንፁህ ዘርን በመጠቀም የሚያደርሰውን ጉዳት መከላከል ይቻላል፡፡

ተባይ

ተልባን ከሚያጠቁት የተባይ ዓይነቶች መካከል የጓይ ትል ዋናው ሲሆን የሚከሰተውም ዝናብ በሚበዛበት ጊዜ ነዉ፡፡ ጓዩን ከነዘሩ በመብላት በምርት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደርሳል፡፡ ኢንዶሳልፋን (Endosulfan 39% E.C.) ኬሚካልን ሁለት ሊትር በሄክታር ሂሳብ በመርጨት ተባዩን መከላከል ይቻላል፡፡

በሽታ

ተልባን ከሚያጠቁት ዋና ዋና በሽታዎች ሦስቱ ተክል አጠውላጊ፣ ፓዝሞና የቅጠል ሻጋታ  ሲሆኑ በሽታዎችን የሚቋቋሙ ምርጥ ዝርያዎችን  በመዝራት፣ ሰብልን በማፈራረቅ፣ በበሽታዉ የተጠቃዉን ገለባ በማቃጠልና በመድሀኒት የታሸ ዘር በመጠቀም በሽታዎቹን መከላከል ይቻላል፡፡

ተክል አጠዉላጊ፡ተክል አጠዉላጊ ተክሉን የሚያጠወልግ የፈንገስ በሽታ ነው፡፡ የአፈር ሙቀትና እርጥበት ከፍ ሲል በከፍተኛ ደረጃ ይከሰታል፡፡ ጉዳቱን ለመከላከል በሽታውን የሚቋቋም ዝርያ መጠቀም ያስፈልጋል፡፡

ፓዝሞ፡ፓዝሞ በአብዛኛው የተክሉን ግንድ የሚለበልብ ነው፡፡ እርጥበት አዘል ሞቃት የአየር ሁኔታ ለበሽታው አምጪ ተህዋሲያን መባባስ አንዱና ዋነኛው ምክንያት ነው፡፡ ሰብልን እያፈራረቁ በመዝራት፣ በፈንገሱ የተጠቃውን ገለባ በማቃጠልና በሽታውን የሚቋቋም ዝርያ በመጠቀም የሚያደርሰዉን ጉዳት መቀነስ ይቻላል፡፡

የቅጠል ሻጋታ፡በጣም እርጥበት ያዘለ የአየር ሁኔታ ለዚህ በሽታ መከሰት መንስዔ ነው፡፡ በሽታውን የሚቋቋም ዝርያ መጠቀም የሚደርሰውን ጉዳት መከላከል ይቻላል፡፡ ሰብልን በማፈራረቅ፣ በበሽታው የተጠቃውን ገለባ በማቃጠልና በመድሀኒት የታሸ ዘር በመጠቀም እንዲሁም ከበሽታ አምጭ ተዋሲያን ነፃ በሆነ አፈር ላይ በመዝራት የቅጠል ሻጋታን መከላከል ይቻላል፡፡