የአመራረት ዘዴዎች


የማሳ ዝግጅት

የተሻለ ምርት ለማግኘት ሦስት ጊዜ ታርሶ በደንብ የለሰለሰና ከአረም የፀዳ ማሣ መሆን አለበት፡፡

የዘር ወቅት

የዘር ወቅት ከቦታ ቦታ ሊለያይ ይችላል፡፡ ሆኖም ወሳኙ ዝናብ የሚጀምርበትና የሚያበቃበት ጊዜ ነዉ፡፡ ለደ/ዘይትና ተመሳሳይ አካባቢዎች ከሰኔ አጋማሽ ጀምሮ እሰከ ሐምሌ መጀመሪያ፣ ለአዋሣ እና  ተመሳሳይ አካባቢዎች ደግሞ ከሐምሌ መጀመሪያ እሰከ ሐምሌ አጋማሽ ድረስ ያለው ተስማሚ የዘር ወቀት ነው፡፡  

የዘር መጠን

የፈረንጅ ሱፍ የዘር መጠን ከ8-12 ኪ.ግ በሄክታር ቢሆን የተሻለ ነዉ፡፡ ዘሩ የሚገኝበት ደረጃም ወሳኝነት ስላለዉ አንደኛ ደረጃ (ግሬድ ኤ) ቢሆን ይመረጣል፡፡  በአጠቃላይ ግን 30 ሳ.ሜ በተክሎች እና 75 ሳ.ሜ ርቀት በመስመሮች መካካል በመጠበቅ ከ44000-50000 ተክሎች በሄክታር ወይም ከ4-5 ተክል በእያንዳንዱ ስኩዌር ካሬ ሜትር ላይ ማምረት ይቻላል፡፡

የማዳበሪያ መጠን

በአገራችን በተደረጉት የፈረንጅ ሱፍ የማዳበሪያ ፍላጎት ጥናት መሠረት ሰብሉ በናይትሮጅንና ፎስፈረስ ማዳበሪያ በምርታማነቱ ላይ የሚያመጣው ለውጥ ያለማዳበሪያ ከተዘራው ጋር ሲነፃፀር አናሳ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ በመሆኑም እስካሁን ድረስ ሰብሉን ያለማዳበሪያ መዝራቱ  በሃገራችን ተመራጭነት ያለው ሆኖ ተገኝቷል ፡፡   

የአጨዳ ወቅት

የፈረንጅ ሱፍ ወደ መድረሻው አካባቢ በወፍ ጥቃት በጣም ስለሚረግፍ  እንደብዙዎቹ የቅባት ሰብሎች በአጨዳ ወቅት ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡ የሰብሉ ትክክለኛ የአጨዳ ወቅት የሚባለዉ ፍሬ አዘሉ ጭንቅላት ከበስተጀርባ በኩል ያለዉ አካሉ ከአረንጓዴነት ወዳ ብጫነት ሲለወጥና በፍሬዎቹ ዙሪያ የሚገኘዉ ቅርፊት /  Bract / መሳዩ ክፍል ወደ ቡኒነት ሲለወጥ ነው፡፡ በዚህ ጊዜ እየቆረጡ ፀሐይ ላይ ማስጣትና የዘሩ እርጥበት ከ9 በመቶ በታች እስከሚወርድ ማድረቅ እጅግ አስፈላጊ ነዉ፡፡  

ውቂያና ክምችት

የፈረንጅ ሱፍ ከመወቃቱ በፊት በአውድማ ላይ የዘር እርጥበቱ 9 በመቶ እስኪደርስ ድረስ መድረቅ ይኖርበታል፡፡ ሲወቃም በአውድማ ላይ በዱላ ወይም በበሬ ወይም በመዉቂያ ማሽን ሊሆን ይችላል፡፡ የፈረንጅ ሱፍ ከተወቃ በኋላ የዘር እርጥበቱ ከ 8 በመቶ  በታች ሆኖ ንፁህ፣ደረቅና ነፋሻ በሆነ ማከማቻ (ጎተራ) ውስጥ መቀመጥ አለበት፡፡

የተሻሻሉ ዝርያዎች

የፈረንጅ ሱፍ ምርታማነትን ለመጨመር በተደረጉ ሙከራዎች እስከአሁን አንድ ዝርያ ብቻ ለተጠቃሚው የተለቀቀ ሲሆን በተጨማሪ አራት ተስፋ ሰጪ የሆኑ በቅርቡ ይለቀቃሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡