የማምረቻ ወቅት
የቲማቲምን የማምረቻ ወቅት ከሚወስኑት ነገሮች ውስጥ ጥቂቶቹ የአየር ንብረት፣ የአፈር ባህርያትና የገበያ ሁኔታ ናቸው፡፡ ቲማቲምን ዓመቱን በሙሉ ማምረት ይቻላል፡፡ ሆኖም በአብዛኛው በዝናብ ወቅት ከፍተኛ የበሽታ፣ የተባይና የአበባ መርገፍ ችግር ስለሚኖር መድሐኒት መጠቀም፣ ለተክሎች ድጋፍ መስጠትና ልዩ ልዩ እንክብካቤዎችን ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ በበጋ አልፎ አልፎ መጠነኛ የበሽታ እና የተባይ ችግር ቢኖርም በመድሐኒት ርጭት ጥሩ ምርት ማግኘት ይቻላል፡፡
ችግኝ ዝግጅት
ቲማቲም በቀጥታ ማሳ ላይ ሊዘራ ወይም ችግኙ ወደ ማሳ ሊዛመት ይችላል፡፡ ሁለቱም ዘዴዎች የተለያየ ጥቅም አላቸው፡፡ በአሁኑ ወቅት ገበሬው ካለው የአመራረት ልምድና የዘር እጥረት አካያ ችግኝ ማዛወሩ ተለምዷል፡፡ ለችግኝ ዝግጅት የሚሆነው ቦታ አፈሩ ውሃ የማይቋጥር፤ ለምነት ያለው፤ ንፋስ፣ በሽታና ተባይ የማይበዛበት ቢሆን ይመረጣል፡፡ አንድ ሄክታር ቲማቲም ለማምረት ጥሩ የመብቀል ችሎታ ያለው (ቢያንስ 95 በመቶ የብቅለት መጠን) ከ300 – 380 ግራም ዘር ያስፈልጋል፡፡ የችግኝ መደቡ በ1 ስፋትና ከ5 እስከ 10 ቁመት ይዘጋጃል፡፡ ዘሩ ትንሽና ቀላል በመሆኑ ለመዝራት ችግኝ ላይ በተመጣጠነ ሁኔታ ለመበተን እንዲያስችል ከአሸዋ ጋር በመደባለቅ በ15 ሴን+ ስፋትና ከአንድ ሴንቲሜትር በማይበልጥ ጥልቀት ቢዘራ ጥሩ ውጤት ይሰጣል፡፡ ዘሩ አፈር ከለበሰ በኋላ መደቡን ሳር በማልበስ ውሃ ማጠጣት ተገቢ ነው፡፡ እንደበቀለ ሣሩን ማንሳት ያስፈልጋል፡፡፡ በቀጣይ ውሃ ማጠጣት ማዳበሪያ መጨመር፣ የሰብል ጥበቃና ሌሎች የችግኝ መደብ ጥንቃቄዎች ማካሄድ ይገባል፡፡ የችግኝን መደብ ማፈራረቅና ጤናማ ችግኝ ማግኘት አስፈላጊ ነው፡፡