የደረቀና የታጠበ ቡና አዘገጃጀት


የቡና አዘገጃጀት ዘዴዎች በሁለት ይከፈላሉ፡፡ እነሱም ያልታጠበና የታጠበ ቡና አዘገጃጀት ናቸው፡፡

ያልታጠበ (የደረቅ ቡና) ዝግጅት

ያልታጠበ ቡና ዝግጅት ከቀይ እሸት ቡና ለቀማ ጀምሮ የሚከተሉት ደረጃዎች አሉት፡፡

ቀይ እሸት ቡና መልቀም

በጥሩ ሁኔታ  የቀላ እሸት ቡና መልቀም፡፡ በተለቀመ ቡና መካከል በአጋጣሚ ወይም በሥራ ጫና ምክንያት ያልበሰሉ ወይንም በመድረቅ ላይ ያሉ ቡናዎችን፣ ቅጠላ ቅጠሎችንና ሌሎች ባዕዳን ነገሮችን ከገቡ ለይቶ ማስወገድ፡፡

የተለቀመውን ቀይ እቺት ቡና ማድረቅ

ቡናን ለማድረቅ ከመሬት 8ዐ ሣ.ሜ. ከፍታ  ያለው ቆጥ መሥራት ተገቢ ነው፡፡ ይህንንም ከወንፊት ሽቦ፣ ከሳጠራ፣ ከሠሌን ወይንም ከተመሣሣይ ነገሮች መሥራት ወይም ከሲሚንቶ (ከኮንክሪት)የተሠራ አውድማን በአማራጭነት መጠቀም ይቻላል፡፡ በቆጥ ወይም በኮንክሪት ወለል ላይ በፀሐይ ብርሃን አማካይነት እንዲደርቅ የተሰጣ ቡናን በየጊዜው በእጅ ማገለባበጥና እርጥበት እንዳይነካው ዘወትር ማታና በዝናብ ጊዜ ላስቲክ ማልበስ ተገቢ ነው፡፡ ቡናን በአፈር ወይም አመድ ላይ በእበት በተለቀለቀ አውድማ ላይ፣ በአስፓልት እና መሰል ነገሮች ላይ ማድረቅ ጣሙንና ጥራቱን ያበላሻል፡፡

የታጠበ ቡና ዝግጅት

ቀይ እሸት ቡናን መልቀም

የሚለቀመው እሸት ቡና የበሰለና ቀይ መሆን አለበት፡፡ በለቀማ ወቅት በቂ የሆነ ሙስሌጅ ወይም አምለግላጊ (Mcilage) እንዲኖር ሙሉ በሙሉ የቀላ ቡናን መልቀም ይገባል፡፡ ተለቅሞ ያደረ፣ የጠወለገና በበሽታ  የተጠቃ ቡና መታጠብ የለበትም፡፡ በለቀማ ሂደቱ ቅጠላ ቅጠልና ሌሎች ባዕዳን ነገሮችን መለየት ይገባል፡፡

መፈልፈል

በፍልፈላ ጊዜ ቀዩ የቡና ገለባ ከሌላው የቡና አካል ይለያል፡፡ በቡኬት ሂደት የሚፈጠሩ የኬሚካል ለውጦች፣ ባዕዳን ንጥረ ነገሮች፣ ብናኞች፣  ኬሚካሎች ወዘተ.. ቀደም ብሎ በመፈልፈያ መሣሪያ ወደተጎዱ ቡናዎች በቀላሉ በመግባት የቡናውን ጥራት ይቀንሳሉ፡፡ ስለሆነም በመፈልፈል ሂደት የሚከሰት የቡና መሰባበርን መከላከል ተገቢ ነው፡፡ ይህንንም ለማድረግ የመፈልፈያ ዲስኩን ማስተካከል ያስፈልጋል፡፡

የቡና ቡኬት

  • ይህ ሂደት አምለግላጊ ተብሎ የሚታወቀውንና የሚያጣብቀውን ጣፋጭ ነገር ከቡናው በቀላሉ ታጥቦ እንዲለይና ወደ ትናንሽ ክፍል አካሎች እንዲቀየር ያደርጋል፡፡
  • አምለግላጊው ያልታጠበ ቡና ጥራቱ ይቀንሳል፡፡
  • ለደቂቅ ተህዋስያን ምቹ መራቢያ ይሆናል፡፡
  • በቡና አደራረቅ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ያስከትላል፡፡
  • አቧራና ብናኝ ነገሮችን በቀላሉ ይስባል፡፡
  • በቡና ቡኬት ወቅት ቀይ የቡና ገለባ መኖር የለበትም፡፡ አብሮ ከቦካ ግን ቀይ ቀለም ስለሚለቅ ተፈላጊውን ቡና በማቅላት ጥራቱን ይቀንሳል፡፡

በቡና ቡኬት ላይ ተፅዕኖ የሚያደርጉ ነገሮች

  • ተስማሚ የሙቀት መጠን የሚችሉትን ሰዓት መወሰን፡፡
  • በቡና እጥበት ሂደት ያለው ኮምጣጤነት (PH)  ከ5-6 መሆን፡፡
  • በቡና እጠበት ሂደት ያለው የኢንዛይም መጠን በቂ መሆን፡፡
  • በእጠበቱ ሂደት በቂ የውሃ መጠን መኖር (ያለመኖር)፡፡

የቡና ቡኬት ሂደትን ለማፋጠን የሚረዱ ነገሮች

  • ቡና የተዘፈዘፈበትን ወይም የተቦካበትን ውሃ  በድጋሚ መጠቀም፡፡
  • በደረቅ (ያለ ውሃ) ቡኬት ማካሄድ፡፡
  • በመካከል የሚደረግ እጥበት /ማገላበጥ/፡፡

ቡና መንክር (መዘፍዘፍ)

ቡና ከቦካ በኋላ እንደገና መዘፍዘፍ ያስፈልጋል፡፡ ይህም በቡኬት ሂደት የቀረውን ሙስሌጅና ኮምጣጤ እንዲለቅ ያደርጋል፡፡ የቡናውን መልክ በማሻሻል ከፍተኛ ጣምና ጥራት እንዲኖረው ይረዳል፡፡

የቡና አደራረቅ ደረጃዎች

የላይኛው የታጠበ ቡና ሽፋን የእርጥበት መጠን ከ55-45 በመቶ መሆን አለበት፡፡ በዚህ ወቅት ባክቴሪያን ፈንገሶች ቡናውን ሊያበሰብሱ ስለሚችሉ ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል፡፡

ነጣ ያለ የድርቀት ደረጃ

  • ነጣ ባለ የድርቀት ደረጃ የቡናው የቺርጥበት መጠን ከ45-30 በመቶ ይሆናል፡፡
  • ይህን የእርጥበት መጠን ለማግኘት ሲባል ቡናው ለከፍተኛ የፀሐይ ብርሃን ከተጋለጠ በቡናው ላይ የኬ ሚካል ለውጥ ሊያጋጥምና የጥራት መቀነስ ሊያመጣ ይችላል፡፡
  • ስለዚህ ቡናውን በተቻለ መጠን ለከፍተኛ የፀሐይ ብርሃን ከማጋለጥ መቆጠብ ይኖርብናል፡፡

በመጠኑ ጠቆር ያለ የድርቀት ደረጃ

  • በዚህ ወቅት ቡናው የመጨረሻ የቀለም ደረጃ የሚይዝበት ጊዜ ሲሆን የፀሐይ ብርሃን በከፍተኛ ደረጃ ይፈልጋል፡፡
  • የቡናው የቺርጥበት መጠንም ከ3ዐ-20 ይደርሳል፡፡

በመካከለኛ ጥቁረት የድርቀት ደረጃ

  • ፈጣን የቡና አደራረቅ በሚቆይበት በዚህ ወቅት የቡናውን ክምር በመጨመር ማድረቅ ይቻላል፡፡
  • በዚህ ጊዜ የቡናው የእርጥበት መጠን ከ2ዐ-16 በመቶ ይደርሳል፡፡

በጣም ጠቆር ያለ የድርቀት ደረጃ

  • የመጨረሻ የድርቀት የእርጥበት መጠን በሚደርስበት በዚህ ወቅት ረዘም ላለ ጊዜ በመጋዘን ሊከማች ይችላል፡፡
  • የቡናው የእርጥበት መጠንም ከ16-11 በመቶ ይደርሳል፡፡