የፓፓያ ተክል ፆታ


ፓፓያ የሚባዛው በዘር ሲሆን ሁለት የተለያዩ ፆታዎች አሉት፡፡ የመጀመሪያውና በአብዛኛው ኢትዮጵያ ውስጥ ጥቅም ላይ እየዋለ ያለው ሁለት ፆታዊ ወይም ዳዩሽየስ ( dieocious) የሚባለው የተለያዩ ወንዴና ሴቴ ዛፎች ያሉት ነው፡፡ ፍሬ የሚገኘው ከሴቴ ተክል ብቻ ቢሆንም የወንዱ ተክል የሴቴዋን ተክል ፍሬ እንድታፈራና ፍሬዎች ውስጥ የሚገኙት ዘሮች መብቀል እንዲችሉ ያደርጋል፡፡ የወንዴ ተክል ዛፍ ፍሬ የማይሰጥ ሲሆን የሚያገለግለው የወንዴ አበባ ዱቄት  ለሴቴ አበባ ለመስጠት ነው፡፡ በፓፓያ ማሳ ላይ የተወሰኑ ወንዴ ተክሎች መኖር የግድ ቢሆንም የወንዴው ተክል ቁጥር በበዛ ቁጥር በተወሰነ መሬት ላይ የሚገኘውን ምርት ይቀንሳል፡፡ ስለሆነም አንድ የወንዴ ተክል በተስማሚው ቦታ  ከተገኘ ከ5-25 ለሚሆኑ ሴቴ ተክሎች በቂ ነው፡፡ የማዳቀሉ ተግባር በነፋስና በአንዳንድ ነፍሳት አማካይነት ይከናወናል፡፡ ከሁለት ፆታዎች የሚገኙ ፍሬዎች በአብዛኛው ትልልቅና ሞላላ ወይም ድቡልቡል ቅርፅ ያላቸው ናቸው፡፡

ሌላው ዓይነት የፓፓያ ተክል ወንዴና ሴቴ ክፍሎች በአንድ ዛፍና አበባ ላይ የሚገኙበት ሶሎ (solo) የሚባለው ነው፡፡ ይህ ፓፓያ ወንዴና ሴቴ አበባዎች በአንድነት ስለሚገኙ በመስክ ላይ ያሉት ተክሎች ሁሉ ፍሬ ይሰጣሉ፡፡ ችግኝ ለማዘጋጀት የሚያስፈልገው የዘር መጠን ለአንድ ሄክ፺ር አንድ ኪሎ ነው፡፡ የፍሬው መጠን አነስተኛ በመሆኑ ሳይበላሽ የመቆየት ችሎታ አለው፡፡ በትኩስ ለመብላት፣ በፍሪጅ ለማስቀመጥም ሆነ ወደ ውጭ አገር ለመላክ እጅግ በጣም ተስማሚ ነው፡፡

ሶሎና ዳዩሺየስ ዝርያዎች ሳይደበላለቁ ለማቆየት ከፍተኛ ጥንቃቄ መደረግ አለበት፡፡ ስለሆነም ባሁኑ ወቅት የሶሎ ፓፓያ ዝርያን ለመልቀቅ መልካሳ ግብርና ምርምር ማዕከል ከፓዌ፣ ከአረካ፣ ከአዋሳ፣ ቲብላና ከላይኛው አዋሽ አግሮ ኢንዱስትሪ ኢንተርፕራይዝ ጋር በመሆን የፓፓያ ዝርያዎችን መረጣን በማካሄድ ላይ ይገኛል፡፡ ዝርያው ከተለቀቀ በኋላም በተከታታይ ያልተደበላለቀ ዘር ለማምረት የማያቋርጥ ክትትልና ጥንቃቄ ይጠይቃል፡፡