ድህረ ምርት አያያዝ


ምርት መሰብሰብ

የሚመረተው ድንች ለምግብነት ከሆነ ምርቱ መሰብሰብ ያለበት ተክሉ ከደረቀ በኋላ ነው፡፡ ምርቱ ለዘር ከሆነ ግን የክሽክሽን አመጣጥ በማየት ማለትም እንደሁኔታው በአንድ ተክል 2-3 ክሽክሽ ከታየና ከ35-50 የሚመዝኑ የድንች ኮረቶች ከሰጠ ግንዱና ቅጠሉ (haulm) መታጨድ ወይም መነቀል አለበት፡፡ ከታጨደ (ከተነቀለ)ከ14 ቀን በኋላ ምርቱ መሰብሰብ አለበት፡፡ ምርቱ ከተሰበሰበ በኋላ መጋዘን ውስጥ ከመግባቱ በፊት ከድንቹ ጋር ያለውን አፈር ማራገፍና በተባይ የተነኩ፣ በዶማ የተወጉ በበሽታ የተበከሉና ደቃቅ ኮረቶችን መለየትና ማስወገድ ያስፈልጋል፡፡

በድህረ ምርት አያያዝ የሚከሰተውን ብክነት ለመቀነስ ድንች አምራች ገበሬዎች ድንችን ሰብስበው ቤት ውስጥ በመከመር ወይም በበቀለበት ማሣ ውስጥ በመተው ድንችን ለተወሰነ ጊዜ የማቆየት ልምድ አለ፡፡ ይሁን እንጂ በአማካይ ከ33-50% እና ከዚያ በላይ የምርት ብክነት እንደሚከሰት ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡

ድንች በአማካይ ከ7ዐ-8ዐ% ውሃ-አዘል በመሆኑ በሙቀትና በመተፋፈግ፤ የመበላሸት፣ የመበስበስ፤ ጥራቱን የመለወጥና የመብቀል ባህርይ ስላለው የድህረ ምርት አያያዝ ቴከኖሎጂ እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ ምርምሩ ቀጣይነት ያለው ቢሆንም እስካሁን ድረስ በተደረገው ጥናት ለዘር የሚሆን ድንች ከ8-9 ወር፤ ለምግብ የሚሆን እስከ 4 ወር ማቆየት የሚችሉ የድንች ማከማቻዎች  ታውቀዋል፡፡

 የማከማቻ ዘዴዎች

የዘር ድንች ብርሃን በማያስገባ ነፋሻማ በሆነ አነስተኛ ወጪ በሚሰራ መጋዘን (Diiffused light store ) ውስጥ መደርደሪያ ላይ መቀመጥ አለበት፡፡ በዚህ ዘዴ በደጋና በወይና ደጋ ለ8 እና 9 ወር ያለምንም ችግር ማስቀመጥ ይቻላል፡፡ ዘሩም ከ3-4 አረንጓዴና ጠንካራ ጉንቁሎች ስለሚኖሩት ምርታማነቱ ከፍተኛ ነው፡፡ ለምግብነት የሚውል ድንች ግን ብርሃን አልባ በሆነ መጋዘን መቀመጥ አለበት፡፡ ከሥርና ከላይ ለአየር ማስገቢያ ቀዳዳ እንዲኖረው ያስፈልጋል፡፡

የምግብ አጠቃቀም

በሀገራችን በአብዛኛው በከተማም ሆነ በገጠር የተለመደው ቀቅሎና በወጥ መልክ አዘጋጅቶ፤ እንዲሁም ጠብሶ መመገብ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት በክሪስፕ፣ ቺፕስ (ደረቅና ለግላጋ ጥብስ) መልክ የመጠቀም ልምድ በከተማዎች እየተለመደ ነው፡፡ ሆኖም  ከድንች ገንፎ፣ ቅንጬ፣ ፍርፍር፣ ሳንዲዊች፣ ብስኩት፣ ሳንቡሳ፣ ቂጣ፣ እንጀራ፣ ዳቦ፣ ሾርባ፣ ጠላ፣ ጭማቂ ማዘጋጀት ይቻላል፡፡