መግቢያ


ዳጉሳ ከአገዳና ብርዕ እህሎች የሚመደብ አገር በቀል ሰብል ነው፡፡ ሰብሉ በዋናነት የሚመረትባቸው የአገራችን አካባቢዎች ጎጃም፤ ጐንደር፤ ትግራይ፤ ወለጋ፤ ቤንሻንጉል ጉምዝ፤ ኢሉባቡርና ጋሙጎፋ ናቸው፡፡ በአሁኑ ጊዜ የተሻሻሉትን አዳዲስ ዝርያዎች በመጠቀም የሻሸመኔ፣ የአርሲ ነገሌና የአላባ ወረዳዎችም በአጭር ጊዜ ውስጥ ከዋና አምራቾች ተራ ሊሰለፉ በቅተዋል፡፡

ለአገዳና ብርዕ ሰብሎች በየዓመቱ ከሚመደበው የመሬት መጠን ዳጉሳ 5 እጅ የሚሆነውን የሚይዝ ሲሆን ይህም በአማካይ 228ዐዐዐ ሄክታር ነው፡፡ የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ባለሥልጣን መረጃ እንደሚያሳዬው በአገራችን የዳጉሳ አማካይ የምርት መጠን በሄክታር ከ1ዐ ኩንታል አይበልጥም፡፡ ነገር ግን በምርምር የተገኙ ዝርያዎችንና የአመራረት ዘዴዎችን በመጠቀም በሄክታር ከ3ዐ ኩንታል በላይ ለማግኘት እንደሚቻል በምርምር ተረጋግጧል፡፡ ዳጉሳ ሳይበላሽና በተባይ ሳይጠቃ ለረጅም ጊዜ በጎተራ ውስጥ ሊቀመጥ የሚችል ሲሆን ይህም አምራቹ በጎተራ ውስጥ አቆይቶ በፈለገ ጊዜ እንዲጠቀምና በደህና ዋጋ እንዲሸጥ እድል ይሰጠዋል፡፡