የአኩሪ አተር ዕድገት በአካባቢ ሁኔታዎች በጣም ይወሰናል፡፡ ውሀ የሰብሉን ምርታማነት በጊዜም ሆነ በቦታ በዋንኛነት የሚወስን ነው፡፡ በአገራችን ከባህር ወለል በላይ ከ300-2200 ሜትር ከፍታ መብቀል የሚችል ሲሆን፣ ከ1300-1700 ሜትር ከፍታ ባላቸዉ አካባቢዎች ጥሩ ምርት ይገኛል፡፡ በአማካይ ከ23-25 ዲግሪ ሴንቲግሬድ የሙቀት መጠን ያላቸዉ አካባቢዎች ለሰብሉ ዕድገት ተስማሚ ናችው፡፡ ለአኩሪ አተር ዕድገት፣ ለማበብና ፍሬ ለመያዝ የሙቀት መጠን ከ 10 ድግሪ ሰንቲግሬድ በታችና ከ40 ድግሪ ሴንቲግሬድ በላይ የሆኑ አካባቢዎች አይስማሙትም፡፡አኩሪ አተር በቀን እስከ 7.6 ሚሊ ሊትር ወሃ በተክል የሚፈልግ ሲሆን፣ ለጥሩ ምርት በጠቅላላ የሰብሉ እድገት ጊዜ 500 ሚ/ሊትር ዝናብ ይፈልጋል፡፡ በተለይም በብቅለት እና ፍሬ በሚሞላበት ጊዜ ውሀ በጣም አስፈላጊ ነዉ፡፡ በእነዚህ የሰብሉ እድገት ጊዜያት የዝናብ እጥረት መከሰት ምርታማነቱን በከፍተኛ ደረጃ ይቀንሰዋል፡፡ ለሰብሉ ምርታማነት ከ460-1500 ሚ/ሊትር አማካይ አመታዊ የዝናብ መጠንና የተስተካከለ ሥርጭት ያላቸው አካባቢዎች ተስማሚ ናቸው፡፡ አኩሪ አተር በተለያዩ የአፈር አይነቶች ሊያድግ ቢችልም፣ ጥሩ ምርት እንዲሰጥ የአፈሩ ዓይነት ለምና ቀላል አሸዋማ፣ ጠቆር ያለ ሸክላማና አሉቪያል ውሀ የማያቁር መሆን አለበት፡፡ የአፈሩ ኮምጣጠነትም ከ5.5-7.0 የሆነ የበለጠ ይስማማዋል፡፡