የማሳ ዝግጅት


የማሳ ዝግጅት  እንደየአካባቢው ሁኔታዎች አመቺነት፣ እንደ አፈሩ ባህሪይና በማሳ ዝግጅት ሰዓት በውስጡ ባከማቸው የብስባሽ መጠንና የማሳው ተዳፋትነት ደረጃ እየታዬ ሊከናወን የሚችል ነው፡፡ ለምሳሌ በተራቆተ ባዶ መሬት ላይ የሚገኝን አፈር የእርስ በርስ መያያዝና ጓል የመፍጠር ባህሪይ የማያበላሽ የእርሻ ድግግሞሽ ለአፈር ክለት መባባስ ዓይነተኛ መንስዔ ይሆናል፡፡ በተገቢው መጠን በሰብል ቅሪት የተሸፈነ አፈር የእርስ በርስ ተያይዞ የመቆየት ፀባይ እንዲኖረው ሲረዳ፣ በፈጣን ጎርፍ ምክንያት የሚከሰተውን የአፈር ክለትን ቀንሶ የውኃ በአፈር ውስጥ መስረግንና የመከማቸት አቅምን ይፈጥራል፡፡

የማሳ ዝግጅት ለጥሩ የሰብል ዕድገትና አቋም የተመቻቸ እንዲሆን የአፈር ለምነቱና የርጥበት መጠኑ ተስተካክል ከላይኛው የአፈር ሽፋን ከ30-40 ሳ/ሜ ጥልቀት ውስጥ መገኘት ይኖርበታል፡፡ በዝናብ ላይ በተመሰረተ የግብርና ሥራ የዝናብ መጠኑ 20 ሚ/ሜ ከሆነ በቂ የርጥበት መጠን ስለሚኖር ሰብል ለመዝራት ይቻላል፡፡ ዘር ከመዘራቱ አስቀድሞ ማሳው በተገቢው ሁኔታ መዘጋጀት አለበት ሲባል ከትላልቅ ጓልች የፀዳ ነገር ግን በድግግሞሽ እርሻ ምክንያት የተፈጥሮ ባህሪው ያልተጎዳ አፈር መሆን ይገባዋል፡፡

በበሬ ማሳ ማዘጋጀት

የማሳው ዝግጅት የሚጀመረው ቀዳሚው ሰብል እንደተነሳ የአፈር ርጥበቱ ሳይጠፋ ማከናወን ይገባል፡፡ እንደ ዝናብና የአረም መብቀል ሁኔታ ከ3-5 ጊዜ ማረስ ያስፈልጋል፡፡  የእርሻውን ምልልስና ጊዜ በማሳደግ አስቸጋሪ አረሞችን ለመቆጣጠር እንዲረዳ ሆኖ መከናወን አለበት፡፡ በደንብ የለሰለሰ ማሳ በአፈር ውስጥ የአየርና የውሃ እንቅስቃሴን ስለሚያሻሽልና የተለያዩ የአረም ዘሮችን ለመቆጣጠር ስለሚያስችል ነው

በትራክተር ማሳ ማዘጋጀት

ዘመናዊ የእርሻ ትራክተር የምንጠቀም ከሆነ እንደ ዝናቡ ሁኔታ ከ1-2 ጊዜ በማረስ ከስክሶ መዝራት ይቻላል፡፡ የአፈር ርጥበት ከማለቁ በፊት የመጀመሪያውን እርሻ ማካሄድ፣ የዘር ወቅት ሲቃረብ ጓሉን መከስከስ ከዘር በፌት የበቀሉ አረሞችን ለማጥፊትና ዘሩ ለስላሳ አፈር አግኝቶ በፍጥነት እንዲበቅል አንድ ዙር በድጋሚ መከስከስ አስፈላጊ ነው፡፡  ማሳው ውሃ እንዳያቁር በተቻለ መጠን በደንብ ደልድሎ ማዘጋጀትና ማንጣፈፍ ወሳኝ ነው፡፡

ውሃ የሚያቁር አፈር ላይ ማሳ ማዘጋጀት

የውሃ ማቆር በሚከሰትበት በጥቁር ኮትቻ አፈር ላይ ወርዱ ከ8-12 ሳ.ሜ እና የማጠንፈፌያ ቦይ ከ15-20 ሳ.ሜ የሆነ ሰፊ መደብ ማውጫ (አይበር ቢ.ቢ.ኤም) መጠቀም ያስፈልጋል፡፡ ማሳውም ከዘር በፊት ቦይ ሊዘጋጅለት ይገባል፡፡

ተዳፋት በሆነ መሬት ላይ ማሳ ማዘጋጀት

ማሳው ተዳፋት ከሆነ የአፈር መከላትን ለመከላከልና በጥሩ ሁኔታ ማሳው እንዲንጣፈፍ ከ2-5 በመቶ የተዛመመ ቦይ መሠራት አለበት፡፡