ጤፍ አገር በቀል በመሆኑ ዝርያዎችን ለማሻሻል የሚደረገው ጥረት ኢትዮጵያ ውስጥ በኢትዮጵያውያን ብቻ ነው፡፡ የተሻሻሉ ዝርያዎችን ለማፍለቅ መነሻ የሚሆነው ብዝሀ-ዘር (ጀርምፕላዝም) የሚገኘውም ከኢትዮጵያ ብቻ ነው፡፡ ዝርያዎችን የማፍለቁ ሥራ ላለፉት 4ዐ ዓመታት የተካሄደ ሲሆን የተገኙት ዝርያዎችም በገበሬው ዘንድ በጥቅም ላይ ውለዋል፡፡ በዚሁ መሠረት ደብረ ዘይት ግብርና ምርምር ማዕከል እስከ አሁን ድረስ ከሀገር ውስጥ ብዝሀ-ዘሮችን በማሰባሰብ፣ መረጣ በማድረግና በማዳቀል 17 የተሻሻሉ የጤፍ ዝርያዎችን በምርምር በማውጣት ለተጠቃሚው እንዲዳረሱ አድርጓል፡፡ የዝርያዎቹ ዓይነትና ተስማሚ አካባቢዎች በሠንጠረዥ 1 እና 2 ላይ ተመልክቷል፡፡ ከዝርያዎች መካከል ፀደይ፣ ገራዶ፣ ቀይ ጤፍና አማራጭ ለዝናብ አጠር አካባቢዎች ተስማሚ ሲሆኑ የቀሩት ደግሞ በቂ ዝናብ ባላቸው አካባቢዎች ሊመረቱ ይችላሉ፡፡