ፓፓያ በተለይ የቫይታሚን ኤ ይዘቱ ከፍተኛ በመሆኑ በቫይታሚን አናሳ የሆነውን የአብዛኛውን ሕዝብ ምግብ የተመጣጠነ ለማድረግ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል፡፡ የማዕድን በተለይ የካልስየም ይዘቱም ከፍተኛ ነው፡፡ ፓፓያ ሆድን የማለስለስ ባሕሪ አለው፡፡ ፍሬው ትኩሱን ወይም ተጨምቆ ብቻውን ወይም ከሌሎች ፍራፍሬዎች ጋር በመቀናበር ለስላሳ መጠጥ፣ ማርማላትና ሌሎች ውጤቶች ይሠራበታል፡፡ ያልበሰለ የፓፓያ ፍሬ ተቀቅሎም ሆነ በሌላ ዘዴ ተዘጋጅቶ ጥቅም ላይ ይውላል፡፡ ፓፔን የሚባለው ከፓፓያ ፍሬ የሚገኘው ውሑድ ነጩ ፈሳሽ ምግብን ለማዋሃድና በበርካታ ስጋ ማቀነባባሪያዎች ከፍተኛ ተፈላጊነት አለው፡፡ ፓፓያን በማምረትና በዘመናዊ ድህረ ምርት አያያዝ፣ ለሀገር ውስጥና ለውጭ ገበያ በማቅረብና እንዲሁም ፓፓያን በማዘጋጀት በተለያየ መስክ ለተሰማሩ ሰዎች የሥራ ዕድል ያስገኛል፡፡ የፓፓያ ቅጠል፤ ፍሬና ዘርም የተለያዩ ጠቀሜታዎች አላቸው፡፡