ማሳ ዝግጅትና ችግኝ ማዛመት


እንደማንኛውም ሰብል የቲማቲም ማሳ ተደጋግሞ መታረስና መለስለስ አለበት፡፡ ማሳው ከተስተካከለ በኋላ ለውሃ ማጠጫ የሚያመች ቦይ በአንድ ስፋት ይዘጋጃል፡፡ ችግኙ ከ13 – 15 ሴ.ሜ ቁመት ሲያድግ ወይም ከ2 – 3 ቅጥል ሲያወጣ ወይም ከተዘራ ከ25 – 30 ቀናት ሲሆነው ወደ ማሳ ማዛመት ያስፈልጋል፡፡  

በጣም ትንንሽና ትልልቅ ችግኞችን መትከል በምርት ላይ ትልቅ ተጽዕኖ ይኖረዋል፡፡ ጤናማና ጠንካራ ችግኝ ከመደብ ላይ በመምረጥና በጥንቃቄ በመንቀል ማሳ ላይ በ100 ሳ.ሜ መደብ ስፋትና በ30 ሳ.ሜ የችግኝ እርቀት ማዛመት ይቻላል፡፡ የማዛመቱ ሥራ ጥዋትና ወደ ማታ  ቢሆን ይመረጣል፡፡  ችግኞቹ ከተተከሉ በኋላ አፈሩን በሥሮቹ ዙሪያ በሚገባ መጠቅጠቅ ችግኞቹ እንዲጸድቁ ይረዳል፡፡

ድጋፍ

የቲማቲም ተክልን መደገፍ መድሐኒት ለመርጨት፣ ውሃ ለማጠጣት፣ ምርት ለመሰብሰብና ልዩ ልዩ የመስክ ሥራዎችን ለመሥራት አመቺ ሁኔታን ይፈጥራል፡፡ ይህ ዘዴ ለመለስተኛ ልማትና በዝናብ ወቅት ለማምረት ከፍተኛ ጠቀሜታ  ይኖረዋል፡፡ ረጃጅም ዝርያዎችን በድጋፍ በማልማት ምርት በብዛትና በጥራት ማሳደግ ይቻላል፡፡ ሆኖም ተጨማሪ ስለሚጠይቅ የድጋፉ እንጨት በተመጣጠነ ዋጋ ለማቅረብ በሚቻልበት ሥፍራ የቲማቲም አምራቾች እንዲጠቀሙበት ይመከራሉ፡፡