አረሞች የሰብሎችን ቦታ፣ የፀሃይ ብርሃን፣ ውኃና ከአፈር ውስጥ የምግብ ንጥረ ነገሮችን በመሻማት ከፍተኛ የምርት ቅነሳ ያስከትላሉ ወይም በሰብሉ ላይ አላስፈላጊ የሆነ ጎጂ ንጥረ-ነገር በስሮቻቸው አማካኝነት በመልቀቅ ዕድገታቸው እንዲገታ ያደርጋሉ፡፡
አረሞች ከምርት ቅነሳም በላይ በተለያየ መንገድ ጎጂ ሊሆኑ የሚችሉበት ሁኔታ አለ፡፡ ይኸውም በአረም ጥቃት የደረሰበት የሰብል ምርት በገበያ ላይ ተፈላጊነቱ ስለሚቀንስ ዋጋው ሊረክስ ይችላል፣ ለምሳሌ እንደ ጅብ ሽንኩርት፣ ሲናር፣ አሰንዳቦ የመሳሰሉት የአረም ዘር ዓይነቶች በኢትዮዽያ የስንዴ ማሳዎች ውስጥ በሰፊው ተሰራጭተው ስለሚገኙና በእነዚህ ማሳዎች ላይ የተመረተው ስንዴ የደቄት ጣዕሙ የተበላሸ ስለሚሆን በዱቄት ፋብሪካዎች ተፈላጊነት አይኖረውም፡፡
በኢትዮዽያ የሚመረተው የመኸር ስንዴ ከፍተኛ የሆነ የአረም ጥቃት የሚደርስበት በመጀመሪያው የሰብሉ የዕድገት ደረጃ ስለሆነ ቀደም ብሎ የአረም መከላከል ስራ መከናወን ይኖርበታል፡፡ ይህም ወሳኝ የአረም መከላከያ ወቅት ከመጀመሪያው የቡቃያ ብቅለት ጊዜ ጀምሮ እስከ መጀመሪያው የአንጓ መራዘም ድረስ ባለው የዕድገት ደረጃ ማለትም በመጀመሪያዎቹ 40 እና 50 ቀናት ውስጥ መሆን ይገባዋል፡፡
በሃገራችን በብዛት የአረም መከላከል ስራ የሚከናወነው በእጅ ነው፡፡ ይህንን ዓይነት የመከላከያ ዘዴ ተመራጭ የሚሆነው የአረሙ ክስተት በዝቅተኛ ደረጃ ለሚገኝና የማሳው ስፋት አነስተኛ ለሆነ ብቻ ሊሆን ይችላል፡፡ አረምን በእጅ መከላከል ውጤታማ የሚሆነው ለቅጠለ ሰፋፊ አረም ዝርያዎች እንጂ ከስንዴው ቡቃያ ጋር ተመሳስለው ለሚወጡት የሳር ዝርያ አረሞች አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል፡፡ የሳር ዝርያ አረሞችን በእጅ በማረም ዘዴ የምንከላከል ከሆነ ዘሩ የተዘራው በመስመር መሆን ይኖርበታል፣ ምክንያቱም ከስንዴው ቡቃያ ጋር ተመሳስለው ከመስመሩ ውጭ የወጡት ዕፅዋቶች በሙሉ እንደ አረም ስለሚቆጠሩ በቀላሉ ለማስወገድ ይቻላል፡፡
ለአርሶ አደሮች ሰብልን ከአረም ወረርሽኝ ጥቃት መከላከል መደበኛ የግብርና ሥራ እንቅስቃሴ እንደሆነ የሚታወቅ ተግባር ሲሆን አረምን ለመከላከል ሲባል ኬሚካልን ከመጠቀም በፊት የተቀናጀ ተባይ መከላከያ ዘዴን ተጠቅሞ በአረም የሚደርሰውን ጥቃት ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ማድረስ ተገቢ ነው፡፡ ከዚህም የመጀመሪያውና ቁጠባዊ የመከላከያ ዘዴው ከአረም ዘር ነፃ የሆነ ዘር መጠቀም ነው፡፡ በአረም የተበከለ በተለይም መምጫውና መከላከያው ያልታወቀ አዲስ ዓይነት መጤ የአረም ዝርያ ያለበትን የስንዴ ዘር ገዝቶ በአዲስ ማሳ ላይ ለመጠቀም መሞከር ለኪሳራ የፈሰሰ መዋዕለ-ንዋይ ነው፡፡
የሚከሰት የአረም ወረርሽኝን በተሳካ ሁኔታ ለመቀነስ ከተፈለገ የእርሻ መሬቶች ጦም በሚያድሩበት ዘመን የሚበቅሉትን አረሞች ዘር ከመተካታቸው በፊት ከማሳው ውስጥ ማስወገድ፣ ለዘር የተዘጋጀው ማሳ ዘር ከመልበሱ በፊት በሚፈጠረው ምቹ ሁኔታ የአረም ዘሮች እንዲበቅሉ ለተወሰኑ ቀናት ጊዜ መስጠትና በእርሻ አማካኝነት ገልብጦ ዘሩን መዝራት ነው፡፡ ይህ በሚደረግበት ጊዜ ሰብሉ የዘር ወቅት እንዲያልፍበትና በዝናብ መቋረጥ ምክንያት ምርታማነቱ እንዳይቀንስ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡
ከዚህ በተጨማሪም በማሳ ውስጥ ያሉትን የአረም ዘሮች ክምችት የሰብል ፈረቃን በማካሄድ መቀነስና መቆጣጠር ይቻላል፡፡ ከስንዴ ሰብል ጋር ተመሳሳይ የብቅለት ዑደት ያላቸው የአረም ዝርያዎችን ለመቆጣጠር በጣም አስቸጋሪ ሲሆን ለምሳሌ ሲናር አንዱና በጣም አስቸጋሪው የብርዕ ሰብሎችን የሚቀናቀን የአረም ዝርያ ነው፡፡ ስለዚህ የሰብል ፈረቃ በምናከናውንበት ጊዜ አዲስ የሚዘራው የሰብል ዓይነት የህይወት ዑደቱ አረሙ ከለመደው የሰብል ዓይነት የተለየ በመሆኑና እንክብካቤም ከተለመደው ስለሚለይ በቀላሉ ለመቆጣጠር ያስችላል፡፡ ለምሳሌ ስንዴን ከባቄላ፣ ከሽምብራ፣ ከበቆል፣ እንዲሁም ከማሽላና ከሌሎች የሰብል ዓይነቶች ጋር አፈራርቆ በመስመር በመዝራት በእጅ ወይም በመሳሪያ በማረም መከላከል ይቻላል፡፡ አረምን በአግባቡ ሳናስወግድ የሰብልን ምርታማነት ለማሻሻል ሲባል በምንጨምረው ማዳበሪያ ይበልጥ ተጠቃሚው አረሙ ስለሚሆን የሰብሉን ምርታማነት በእጅጉ ይጎዳዋል፡፡
ስንዴን በመስመር ወይም በቦይ መካከል በ30 ሴ/ሜ ርቀት በእጅ ወይም በመዝሪያ ማሽን መዝራት የሚቻል ሲሆን ይህም አንዱና አዋጭ የአረም መቆጣጠሪያ ዘዴ ሆኖ ሊወሰድ ይችላል፡፡ በመስመር የተዘራ የስንዴ ቡቃያ መብቀል እንደጀመረ በተዘራበት መስመር መካከል የበቀሉትን አረሞች በኩትኳቶ በቀላሉ ማስወገድ ይቻላል፡፡ ትክክለኛውንና ተገቢውን እንክብካቤ እስካከናወንን ድረስ ሰብሎችን አሳስቶ ወይም አራርቆ በመዝራት ምክንያት የሚከሰት የምርት ቅነሳ ሊመጣ እንደማይችል ቀደም ሲል ከተከናወኑ የሙከራ ስራዎች ግንዛቤ ተወስዷል፡፡
አረሞችን በኬሚካል መከላከል ሌላው ዘዴ ሲሆን እነዚህ ኬሚካሎች እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1940 ዎቹ ገደማ 2-4 ዲ፣ ኤም.ሲ.ፒ.ኤ እና ሌሎች ፌኖክሲ የተባለና ዕፀዋትን መርጠው ሊገድሉ የሚችሉ ውሁዶች መፈብረክ ጀመሩ፡፡ እነዚህ ኬሚካል ውህዶች ዓመታዊዎቹን ብቻ ሳይሆን አንዳንድ ቋሚ የሆኑ የአረሞች ሰውነት ውስጥ ፈጥነው በመሰራጨት መግደል ችለዋል፡፡ ይሁን እንጂ አረሞችን በኬሚካላዊ ዘዴ ብቻ መከላከል እንደ ብቸኛ መፍትሄ መውሰድ ሳይሆን እንደ ተጨማሪ አማራጭ አድርጎ መውሰድ ተገቢ ነው፡፡ በአረም ማጥፉያ ኬሚካሎች ብቻ መተማመን ለሌሎች አረምን የመከላከያ ዘዴዎችን ማለትም መቁረጥና በእጅ ማረምን በመተው ሊያዘናጋ ስለሚችል በኬሚካል ላይጠፉ የሚችሉ አረሞች እንዲስፋፉ መንገድ ይከፍታል፡፡ ይህንን ችግር ለመቀነስ የሰብል ፈረቃ መጠቀምና የተለያዩ ዓይነት የፀረ-አረም ኬሚካል ውህዶችን ወይም የኬሚካል ዓይነቶችን በተለያዩ የሰብል ወቅቶች ማፈራረቅና አዋጭነቱ እየታየ በእጅ ማረም ተገቢ ነው፡፡
እንደ ዲካምባ፣ ፒክሎራን፣ 2-4-ዲ እና ኤም.ሲ.ፒ.ኤ የመሳሰሉት ፀረ አረሞች የአረሞቹን ዕድገት መቆጣጠር የሚያስችል ኬሚካል በውስጣቸው ስለያዘ ቅጠለ ሰፋፊ የሆኑ አረሞችን መቆጣጠር ይችላሉ፡፡ እነዚህ ፀረ-አረም ኬሚካሎች በአረም ቅጠሎች ላይ እንደተረጩ በፍጥነት ወደ ስሮቻቸው በመስረግ ዕድገታቸውን ይቆጣጠራሉ፡፡ ሰብሉ ተዘርቶ ከበቀለና ቅጥያዎች ወጥተው እንደተጠናቀቁ የአንጓ ማራዘም ከመጀመሩ አስቀድሞ (ከተዘራ ከ35 እስከ 40 ባሉት ቀናት ውስጥ) የፀረ-አረም ኬሚካል ቢረጭ በሰብሉ ላይ ምንም ዓይነት አደጋ ሳይደርስ አረሞቹን ሊገድል ይችላል፡፡ እዚህ ላይ መጠቀስ ያለበት ነገር ቢኖር ከዚህ በላይ የተዘረዘሩት ፀረ-አረም ኬሚካሎች ሁሉ በበለፀጉት ሃገራት ጥቅም ላይ እንዲይውሉ የተከለከሉ ሲሆን በምትካቸው በአዲስ መ፤ክ የተቀመሩና የዕድገት መቆጣጠሪያ ንጥረ-ነገር የሌላቸው ፀረ-አረም ኬሚካሎች ተፈልስፈዋል፡፡ ይሁን እንጂ 2-4-ዲ አማይን የተባለው ፀረ-አረም ኬሚካል በዋጋው ዝቅተኛነት የተነሳ ከረጅም ጊዜ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ በሀገራችን ውስጥ በሰፊው ይሰራበታል፡፡ በዚህም ምክንያት አንዳንድ ቅጠለ ሰፊፊ የአረም ዝርያዎች ባህሪያቸውን በመቀየርና ፀረ-አረም ኬሚካሉን በመቋቋም በቀላሉ ለመቆጣጠር በማያስችል ደረጃ ላይ ስለደረሱ የፀረ-አረም ኬሚካል ጎጂ ጎን ሰለባ መሆን አይቀሬ ሆኗል፡፡ ይህንን ችግር ለመቋቋም በአሁኑ ጊዜ 2-4-ዲን ከመርጨት አስቀድሞ የዕድገት መቆጣጠሪያ ሆርሞን አልባ የሆኑትንና በንግድ ሥማቸው የሚጠሩትን ኬሚካሎች እንደ ብሪቶክስ፣ ስታሬን ኤም፣ ባሳግራን፣ ግራንስታር፣ ወዘተ የመሳሰሉትን መጠቀም የግድ ብሏል፡፡ የእነዚህ ፀረ-አረም ኬሚካሎች የአጠቃቀም ሁኔታን በተመለከተ በመያዣቸው ላይ የተዘጋጀውን መመሪያ በሚገባ በመከታተል እንደ አረም ክስተቱ ደረጃ፣ የሚረጭበት ጊዜና ለመከላከል የምንፈልገው የአረም ዓይነት ሊወሰን ይችላል፡፡
የሳር ዝርያ የሆኑና እንደ ሲናር፣ አስንዳቦ እና ሌሎችም ሳሮች በአንዳንድ አርሶ አደር ማሳዎች ውስጥ በወረርሽኝ መልክ በመከሰታቸው ምክንያት በስንዴ ምርት ላይ አስደንጋጭ አደጋን ደቅነዋል፡፡ እነዚህን የሳር ዝርያ አረሞች ለመከላከል የሚያስችሉ ቶፒክ እና ፓላስ የተባለ ውጤታማ መርጦ ገዳይ ፀረ-አረም ኬሚካሎችን በመርጨት መቆጣጠር ቢቻልም ዋጋቸው ከፍተኛ በመሆኑ ምክንያት አርሶ አደሮች በእጅ የማረም ዘዴን ለመጠቀም ተገደዋል፡፡ በዚህም ምክንያት በመርጦ ገዳይ ኬሚካል ሳይሞቱ የመቋቋም ባህሪ ያመጡ አረሞች በቡቃያ የዕድገት ደረጃ ላይ ከስንዴው ሰብል ጋር ስለሚመሳሰሉና ለመለየትም ስለሚያስቸግሩ የአረም ማረም ተግባር የሚከናወነው በጣም ዘግይቶ አረሙና ሰብሉ የሚለይበት ደረጃ ላይ በመሆኑ በሰብሉ ምርታማነት ላይ ጥቃት ከደረሰ በኋላ ነው፡፡
ሠንጠረዥ 4፡ የስንዴ አረምን ለመቆጣጠር የሚረዱ የተለያዩ ፀረ–አረም መድሃኒቶች አይነትና የርጭት መጠንና ጊዜ
ዓይነት | የፀረ-አረሙ ስም | መጠነ (ሊ/ሄክታር) | የሰብሉ ዕድገት ደረጃ |
ቅጠለ ሰፋፊ | ስታሬን | 2-5 ቅጠሎች | |
ባንቬል | 2-5 ቅጠሎች | ||
ግራን ስታር | 2-5 ቅጠሎች | ||
ደርቢ | 2-5 ቅጠሎች | ||
የሣር አረሞችን ገዳይ (አይመርጤ) | ፑማ ሱፕር | 2 ቅጠሎች ወደ 1 አንጓ | |
ቶፒክ | 3-6 ቅጠሎች | ||
ፓላስ | 3-6 ቅጠሎች | ||
ጠቅላላ አረሞችን ገዳይ (አይመርጤ) | ራውንድ አፕ | 2 | ሰብሉ ሳይዘራ 10-15 ቀናት በፊት አረም በብዛት ሲበቅል |
ስንዴን በመስመር መዝራት የሳር አረሞችን ለመቆጣጠር አመቺ ሁኔታን ይፈጥራል፡፡ በኢትዮዽያ ውስጥ ስንዴን ለመጀመሪያ ጊዜ በመስመር የመዝራት ፅንሰ-ሃሳብ የተጀመረው የሳር አረሞችን በአረም ማረሚያ ማሽን (በበሬ ወይም በአነስተኛ ትራክተር በሚጎተት መሳሪያ) ወይም በእጅ አረማ ለመቆጣጠር ሲባል ነበር፡፡