የስንዴን በሽታ


አፈር ወለድ በሽታ

የስንዴን ሥርና ከአፈሩ አካባቢ የሚገኘውን የታችኛውን የአገዳውን ክፍል የሚያጠቁ በዓይን የማይታዩ ጥቃቅን በሽታ አምጪ ተህዋስያን በአፈር ውስጥ ይገኛሉ፡፡ የእነዚህ ጥቃቅን በሽታ አስተላላፊ ተህዋስያን የተለየ ባህሪ የህይወታቸውን ግማሽ ዘመን የሚያሳልፉት ከአፈር ጋር በቀጥታ በመነካካት መሆኑ ነው፡፡ እነዚህ በሽታ አስተላላፊ ተህዋስያን በሚከተለው አኳኋን በሁለት ሊከፈል ይችላሉ:- 1) የስንዴ ሰብል በሌለበት ጊዜ ሁሉ በአፈር ውስጥ ለብዙ ዓመታት ሊኖሩ የሚችሉና፣ 2) ከሌላ አካባቢ በመምጣት በስንዴ ማሳ ውስጥ የሚኖሩ ሆነው አመጣጣቸው ከሌላ የሰብል ዓይነት ወይም በአካባቢው ከሚገኝ የስንዴ ማሳ ሆኖ በንፋስ፣ በእርሻ መሳሪያዎች፣ በሰውና በእንስሳት አማካኝነት የሚሰራጩ ናቸው፡፡

በአጠቃላይ በሥር አበስብስ የበሽታ ተህዋስያን የተጠቁ ተክሎች የመቀጨጭ፣ ደካማ ቅጥያ ወይም ጭራሽ ያለማውጣት፣ የመቃጠል ፣ የቅጥያዎች ሳይደርሱ መሞት እና የተጨማደደ (በደንብ ያልሞላ) የስንዴ ዘር እንዲኖራቸው ያደርጋል፣ በዚህ በሽታ የተጠቁ ተክሎች አብዛኛውን ጊዜ በማሳው ውስጥ አንድ ቦታ ችምችም በማለት እዚህም እዛም ተበታትነው በግልፅ ይታያሉ፣ የደረሱ ተክልች ማህል አገዳቸው ላይ ቀለሙን የቀየረና የበሰበሰ ምልክት ይታያል፡፡ የበሽታ አምጭ ተህዋስያኑን ምንነት ለይቶ ለማወቅ የላብራቶሪ ምርመራ በማካሄድ ማረጋገጥ ተገቢ ይሆናል፡፡ በሥሮችና የታችኛው የአገዳ ክፍል ላይ የሚከሰተው የመበስበስ በሽታ በሻጋታ አምጭ ተህዋስያን አማካኝነት ሊከሰት የሚችል ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ ፋይተም ስፓ፣ራይዝኮቶኒያ ስፓ፣ሲፓልስፖሪየም ስፓ፣ፉሳሪየም ስፓ፣እና ኒማቶድስ ዋነኞቹ ናቸው፡፡ እነዚህንም ለመከላል ተቋቋሚ ዝርያ መጠቀም፣ ዘርን በፀረ-ሻጋታ ኬሚካል ማሸትና የሰብል ፈረቃን መጠቀም ተገቢ ነው፡፡

የስንዴ ቅጠል፣ ዛላ፣ ባክቴሪያና ሻጋታ በሽታ

ሌሎች ተጠቃሽ ከሆኑት የስንዴ በሽታዎች ውስጥ የቅጠልና የዛላ ምች በሽታ አምጪ ደቂቅ ተህዋስያን ዋነኞቹ ናቸው፡፡ ከነዚህም ውስጥ ቅጠል ቆርምድ እና የዛላ ምች በሽታን የሚያስከትለው ሲፖትሪያ ስፓ የሚባለው ተህዋስያን በዋናነት ተጠቃሽ ነው፡፡ ይህ የበሽታ አምጭ ተህዋስያን ወበቃማና በአማካኝ ከ20-25 ዲግሪ ሴልሼስ የአየር ሙቀት ተስማሚ የእድገት ሁኔታን ይፈጥርለታል፡፡ የበሽታው ልዩ ምልክት በመጀመሪያ የታችኞቹ ቅጠሎች ላይ በመከሰት ጊዜው እየቆየ በሄደ ቁጥር ወደ ላይ በመስፋፋት ዛላው ላይ ይደርሳል፡፡ የተራዘመ ደመናማ የአየር ሁኔታና ዝናብ በሽታ አምጭውን ተህዋስያን በፍጥነት ለማስተላለፍ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራሉ፡፡ ለተደጋጋሚ ጊዜያት ስንዴን እንደ ብቸኛ ሰብል በአንድ በተወሰነ ማሳ ላይ ብቻ የምናበቅል ከሆነ በሽታ አስተላላፊ ተህዋስያኑ በሰብል ቅሪት ላይ በመቆየት በተከታዩ አዲስ ሰብል ላይ ክስተቱ የጎላ ይሆናል፡፡ ለበሽታው ተጋላጭነት የሌላቸውንና የመቋቋም ባህሪ ያላቸውን ዝርያዎች እና ሰብልን አፈራርቆ መዝራት በዝቅተኛ ወጪ በሽታውን የመከሊከያ ዘዴ መሆኑ ከግንዛቤ ሊወሰድ ይገባል ፡፡

አንዳንድ ጊዜ በዛክቴሪያ በሽታ አምጪ ተህዋስያን ምክንያት የቅጠል ምች ረዘም ብሎ ቀጠን ያለ ምልክት ያለው በሽታ በስንዴው ቅጠል ላይ ይከሰታል፡፡ የዚህ በሽታ አምጪ ተዋህስያን ጤነኛ ባልሆነ ዘር አማካኝነት (ዘር ወለዴ) የሚተላለፍ ሲሆን ተህዋስያኑ ግን በስንዴ ቃርሚያ ላይ ህይወቱን አቆይቶ በቀጣዩ ሰብል ላይ ሊከሰት ይችላል፡፡ የባክቴሪያ በሽታ አምጪ ተህዋስያን ከአንዱ ተክል ወደ ሌላኛው ተክል በዝናብ ነጠብጣብ አማካኝነት መተላለፍ የሚችል ቢሆንም በነፍሳትና በንፋስ አማካኝነትም ሊዛመት የሚችልበት እድል አለው፡፡ በመዛመት ተክሉን መበከል የሚችለው የባክቴሪያው መባዣ ክፍል ወደ ተክሉ አካል ሊገባ የሚችለው በተፈጥሮ የመተንፈሻ ቀዲዲዎቹ እና በቆሰለ አካሉ በኩል ነው፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ የበሽታው ክስተት በተክሉ ቅጠል ላይ ሲታይ የቆሰለ፣ በጣም ቀጭንና ውኃ የቋጠረ ምልክት በመሆን ጀምሮ እየረዘመ በመሄድ በቅጠሉ ዳርኛው ጠርዝ ላይ ይደርሳል፡፡ የበሽታ አምጭው ባክቴሪያ ዝናብ ወይም ጤዛ ባለበት ሰዓት በእዥ/ፈሳሽ መልክ ከቆሰለው የተክል አካል ላይ ይፈጠራል፡፡ በእዥ መልክ የፈሰሰውም ባክቴሪያ በስሱ በመድረቅ በስንዴው ቅጠል ወይም ዛላ ላይ ይጋገራል፡፡

ለበሽታው ተጋላጭነት የሌላቸውንና የመቋቋም ባህሪ ያላቸውን ዝርያዎች፣ ንፁህና በመከላከያ ኬሚካል የታሸ ዘር በመጠቀም በሽታውን ለመከላከል ይቻለል፡፡

የበሽታ አምጭና አስተላላፊ ከሆኑት የባክቴሪያ ተህዋስያን መካከል ዛንቶሞናስ ካምፐስትሪሰስ፣ ፔስዱሙናስ ሲሪንጃ፣ፒ.አትሮፋሲንስ እና ኮሪን ባክቴሪየም ትሪቲክ ዋነኛ ተጠቃሾች ናቸው፡፡

የስንዴ ግንድ ዋግ

የስንዴ አገድ ዋግ በሽታ ያለ አንዳች ችግር በስንዴና ከስንዴ ጋር ተዛማችነት ካላቸው የሳር ዝርያዎች ጋር በእድገታቸውም ሆነ በስነ ዑደታቸው ጊዜ ውስጥ አብሮ የኖረ ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ የስንዴ አገዳ ዋግ በሽታ ከጥንትም ጀምሮ እንደነበረ በመፅሃፍ ቅዱስ ውስጥ እንኳን ተጠቅሷል፡፡

የስነ-ምድር ምርምር ማስረጃ እንደሚያመለክተው የስንዴ አገዳ ዋግ በሽታ 1400 ዎቹ ከክርስቶስ ልደት በፊት ሁለ እንደነበረ ከስንዴ ዛላ ቁርጥራጮች/ስብርባሪዎች ላይ በተደረገ የናሙና ጥናት ተረጋግጧል፡፡

የስንዴ አገዳ ዋግ በሽታ አምጪው ተህዋስያን በስንዴ ተክል አገዳ፣ በቅጠሉ ጠርዝና የዛላ ተሸካሚ አንገት ላይ ሊታይ የሚችል የቀይ ቡኒ ቀለም ያለው ምልክት ያሳያል፡፡ የተፈጠረውም ምልክት በሰብሉ ቅጠል ላይ በሁለቱም በኩል (በውስጥና በውጭ) መንጠባጠብ ይጀምራል፡፡ ይህ የስንዴ አገዳ ዋግ በሽታ በተለይ ቀደም ብሎ በሰብሉ እድገት ደረጃ ወቅት በወረርሽኝ መልክ ከጀመረ 100 በመቶ የሚደርስ የምርት ጥፋት ሊያስከትል ይችላል፡፡

የስንዴ አገዳ ዋግ በሽታን ለመከላከል ፀረ-ሻጋታ ኬሚካል ቀደም ብሎ በመርጨት ወይም በሽታውን ሊቋቋሙ የሚችሉ ዝርያዎችን መጠቀም አስፈላጊ ነው፡፡ አንድ ዝርያ ይህንን በሽታ የመቋቋም አቅሙን ማጣት ከጀመረ ከፍተኛ የምርት ኪሳራ በአርሶ አደሮች ላይ ከመድረሱ በፊት ዝርያውን ከምርት ማስወጣት ተገቢ ነው፡፡

የስንዴ ቅጠል ዋግ

በቅጠል ላይ የሚፈጠረው የስንዴ ዋግ በሽታ ምልክት በአገዳው ላይ ከሚፈጠረው የዋግ በሽታ ጋር በእጅጉ ተመሳሳይ ቢሆንም በቀለሙ ግን ደማቅ ብርቱካናማ ወይም ቡናማ በመሆኑ ምክንያት ቡናማ ዋግ ይባላል፡፡ ሌላኛው የስንዴ ቅጠል ዋግ ከአገዳ ዋግ በሽታ ልዩ የሚያደርገው ባህሪ የበሽታ አስተላላፊው ተህዋስያን መራቢያ አካል (ዘር) የሚበተነው ከቅጠሉ የላይኛው ጠርዝ ላይ መሆኑ ነው፡፡ ቀደም ሲል ከተዘረዘሩት ሶስት ዓይነት የስንዴ ቅጠል ዋግ አስተላላፊ ተህዋስያን መካከል ፑኪንያ ሪኮንዲታ ኤፍ ስፓ ትሪክት የተባለው ዝርያ በተለያየና ሰፊ የሆነ የመላመድ ችሎታ ያለው ነው፡፡ በባሕሪውም መካከለኛ የሆነ የሙቀት መጠን ያለበት አካባቢ ስለሚፈልግ በዓለም ዘሪያ የስንዴ ሰብል አምራች የሆኑ አካባቢዎች ሁሉ በስንዴ ቅጠል ዋግ በሽታ ተጠቂ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ይህንን በሽታ ለመከላከል የሚያስችል ፀረ-ሻጋታ ኬሚካሎች በቀጣይ የተዘረዘሩ ቢሆንም በሽታውን ሊቋቋሙ የሚችሉ ዝርያዎችን መጠቀም የተሻለ አማራጭ መንገድ ነው ፡፡

ባለ ሪጋ ቢጫ ዋግ

የበሽታው ምልክት ቢጫ ቀለም በመያዝ በቀጥተኛ መስመር የተሰመረ ሪጋ በተክሉ ቅጠል ላይ ይኖረዋል፡፡ በዚህ ልዩ ምልክት ምክንያት ባለሪጋ ወይም ቢጫ ዋግ በመባል ይጠራል፡፡ የበሽታው አስተላላፊ ተህዋስያን ፑኪና ስትሪ ፎርምስ ቫር፣ ስትሪፎርምስ በመባል የሚለይ ነው፡፡ የበሽታ አስተላላፊው ተህዋስያን መራቢያ አካል (ዘር) ከስንዴው ቅጠሌ ጠርዝ ላይ ወይም ለበሽታው ተጋላጭ በሆኑ የስንዴ ዝርያ ዛላዎች ላይ በመነሳት ሊሆን ይችላል፡፡ ለበሽታ አምጭው ተህዋስያን በጣም ተጋላጭ በሆኑ ዝርያዎች ላይ የምርት ቅነሳው አንዳንዴ እስከ 100 በመቶ ሊደርስ ይችላል፡፡

በሽታውን ለመከላከል በስንዴው አካል ውስጥ ዘልቆ የሚገባ ለአገዳ ወይም ለቅጠል ዋግ በሽታ የምንጠቀመውን ፀረ-ሻጋታ ኬሚካል መርጨት ብንችልም ከሁሉም በላይ ግን በረጅም ጊዜ እቅድ በሽታውን መቋቋም የሚችሉ የስንዴ ዝርያዎችን መጠቀም ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው የላቀ ነው፡፡ ምንም እንኳን የፀረ-ሻጋታ ኬሚካልችን ለስንዴ ዋግ በሽታ መከላከያነት እንደ መጨረሻ የመፍትሄ እርምጃ የሚወሰድ ቢሆንም ባስፈላጊነታቸው ጊዜ በወቅቱ አግኝቶና በአግባቡ ለመጠቀም ያስችል ዘንድ ዝርዝራቸው ለይቶ ማውጣትና ማስቀመጥ አስፈሊጊ የጥንቃቄ ተግባር ነው፡፡

ሠንጠረዥ 5. የስንዳዴ ዋግን መቆጣጠር የሚችል የተለመደ የፀረ-ሻጋታ ኬሚካሎችና የአጠቃቀም መጠን

ፀረ-በሽታ ኬሚካሎችናየአጠቃቀም መጠን ለሄክታርውሃ ሊትር/ሄክታርምርመራ
ቲልት 250 ኢሱ0.5 ሊትር150-200በሽታው ቀማሞ ከተክሉ እና የሚስፋፋ ከሆነ ለሁለተኛ ጊዜ የማፈጨው መድኃኒት መጀመሪያ ከተረጨበት ጊዜ ከ3-4 ሳምንት በኋላ ነው፡፡
ባምፕር 25ኢሱ0.5 ኪ/ግ
ባይልቶን 25 ደብሊዉ ፒ0.5 ኪግ
ኖብል 25 ደብሊዉ ፒ0.5 ኪ/ግ
ኦሪዮስ 25 ኢ ደብሊዉ1 ኪ/ግ
ሬክስ 

ፀረ-ሻጋታ ኬሚካሎችን የሚጠቀሙ አርሶ አደሮች አንድ ዓይነት ይዘት ያለውን ኬሚካል ደጋግመው ከመጠቀም መቆጠብ ይኖርባቸዋል፣ ምክንያቱም ተመሳሳይ ይዘት ያለውን ኬሚካል ደጋግሞ መጠቀም በሽታው ፀረ-ሻጋታ ኬሚካሉን በመላመድ የመቋቋም ችሎታ ሊያዳብር ስለሚችል ነው፡፡ ይህንን ችግር ለመቅረፍ የተለያየ ደረጃና አይነት ያላቸውን ኬሚካሎች እያፈራረቁ ለመጠቀም መሞከር ነው፡፡

የስንዴ አረማሞ

የሃገራችን አብዛኛው አርሶ አደሮች የዘር ምንጭ ስርጭትና ክምችት የሚከናወነው ከማሳ ላይ መርጦ ለብቻው በማቆየት ወይም እርስ በእርስ በመለዋወጥ በመሆኑ ምክንያት አገልግሎት ላይ የሚውሉት ዘሮች በኬሚካል ለመታሸት ያላቸው እድል ዝቅተኛ ስለሆነ በዘር ወለድ የሚፈጠረው በሽታ የአስከፊነት አድማስ እየሰፋ በመምጣቱ በሁሉም የስንዴ አብቃይ ማሳዎች ላይ አንዳንድ በዋግ በሽታ የተጠቁ የስንዴ ዛላዎችን መመልከት የተለመደ ክስተት ሆኗል፡፡ ስለዚህም የሰብል በሽታ ስርጭት ቁጥጥር ስራን አጠናክሮ በመሥራት በፀረ-ሻጋታ ኬሚካል ያልታሸ የዘር ስርጭትን መቆጣጠር ሊተኮርበት የሚገባው ተግባር ነው፡፡ አራት የተለያዩ የስንዴ አረማሞ በሽታ አይነቶች ይገኛሉ እነሱም፡-

  • ሽፍን (ሸታታ) አረማሞ
  • ብትን አረማሞ
  • የባንዲራ አረማሞ
  • የዘር አረማሞ ናቸው፡፡

ሶስቱ የአረማሞ አይነቶች በቀጥታ ዘሩን የሚያጠቁ ሲሆን አንደኛውና ባንዲራ አረማሞ የሚባለው ግን ለአረማሞ በሽታ በቀላሉ ተጠቂ በሆኑ ተክሎች ቅጠል ላይ የሚገኝ ነው፡፡

ሽፍን አረማሞ በሁለት ዓይነት ተዛማጅነት ባላቸው የሻጋታ ዝርያዎች ሊፈጠር የሚችል ሲሆን በሽታውን አስተላላፊው ቲልቲያ ኬሪስ ወይም ቲ ፎቲዳ የሚባሉት ተህዋስያን ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ በዚህ በሽታ የተጠቃ የስንዴ ዛላ ውስጥ የሚፈጠሩት ዘሮች በሙሉ በበሽታ አምጪው ተህዋስያን የዘር አካል ውስጣቸው በመሞላት የዘር አቃፊው የላይኛው ልባሱን አስመስሎ በመልበስ ይታያል፡፡ በዚህ በሽታ የተጠቃ የስንዴ ተክል በእድገቱ የቀጨጨ ሆኖ በዛላው ውስጥ ያሉት የስንዴ ዘሮች በሙሉ ወይም በከፊል በበሽታው የተበከሉ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ከዚህ ከተበከለው ዘር ውስጥ የሚለቀቁት የአረማሞው ተዛማች በሽታ አስተላላፊ ዘሮች የተበላሸ የአሳ ጠረን ያላቸው ስለሆነ በሩቁ ይለያሉ፡፡ በዚህ ሁኔታ የተበከሉት ንፁህ ዘሮችም ቢሆኑ ጥራታቸው ስለሚቀንስ ለዱቄት ፋብሪካዎችም ሆነ ለመኖነት ተፈሊጊነታቸው ዝቅተኛ ነው፡፡ ይህንን የአረማሞ በሽታ በአለም ዙሪያ ከሚመረትባቸው የስንዴ አምራች አካባቢዎች ለመከላከል ፒሲ ኤንቢ የሚባለውን የዘር ማሻ ኬሚካል መጠቀም ተገቢ ነው፡፡ የአረማሞ በሽታ ዘር በተገቢው ሁኔታ በኬሚካል በማይታሽባቸው አካባቢዎች ጉዳቱ የከፋና እየተስፋፋ የሚመጣበት እድል ከፍተኛ ነው ፡፡

ዩስቲላጎ ትሪቲክ በሚባለው በሽታ አምጪ ተህዋስያን አማካኝነት የሚከሰተው ብትን አረማሞ በሃገራችን የስንዴ አብቃይ አካባቢዎች በብዛት የተለመደ ነው፡፡ በሽታው የሚተላለፈው በዘር ውስጥ በማለፍ ነው፡፡ በበሽታው አምጪ ተህዋስያን የተበከለው የስንዴ ዘር መብቀል እንደጀመረ የበሽታው የዘር ፍሬም አብሮ በመብቀል በተክሉ ውስጥ ለውስጥ ሳይታይ ማደግ ይጀምራል፡፡ በመጨረሻም ስንዴው ማዘርዘርና ፍሬ መያዝ በሚጀምርበት ሰዓት ላይ ዘሩን ተክቶ አረማሞው ያድጋል፡፡ በዚህ መልኩ እራሱን በስንዴው ዘር የተካው የአረማሞ ዘር በንፋስና በዝናብ አማካኝነት እየቦነነ በጤነኞቹ የስንዴ ማሳዎችና ተክሎች አበባ ላይ በመጣበቅ ለመጪው የሰብል ዘመን በአዲሱ የስንዴ ሰብል ውስጥ የብከላ ህይወት ኡደቱን ይቀጥላል፡፡ በሽታውን በብቃት ለመከላከል ዘርን ካርቦክሲል እና ቤኖማይል በሚባሉ በዘዴ ፀረ-ሻጋታ ኬሚካል ማሸት ያስደልጋል፡፡

ሌሎች የስንዴ በሽታዎች

ምንም እንኳን በሃገራችን የስንዴ አብቃይ አካባቢዎች የተለመደ ባይሆኑም እንደ አመዳይና ቫይረስ የመሳሰሉትን የበሽታ አምጪ ተህዋስያን ጠቅሶ ማፉ አስፈላጊ ሊሆን ይችላል፡፡

ለምሳሌ ዱቄታማው የአመዳይ በሽታ በሰሜን አውሮፓ፣ ራሺያ፣ የአሜሪካና ካናዳ ቀዝቃዛ አካባቢዎች የሚታወቅ ነው፡፡ በነዚህ አካባቢዎች በክረምቱ ወቅት የሚዘራው የስንዴ ሰብል በፀደይ ከሚዘራው በበለጠ ሁኔታ ለበሽታው ተጋሊላጭ ነው፡፡ የበሽታውን አስተላላፊ የሚሆነው ተህዋስያን በግዥ መልክ ወደ ሃገር ውስጥ በሚገባው ስንዴ አማካኝነት አብሮ በመግባት በተለይ በቀዝቃዛ አካባቢዎች ለሚዘሩ የስንዴ አብቃዮች መነሻ እንዳይሆን ጥንቃቄ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡

በቫይረስ አማካኝነት የሚከሰቱትን የስንዴ በሽታዎች ለመጥቀስ ያህል አጭር የገብስ ቢጫ ቫይረስ (ቢዋይዲቪ) እና ሰረዝማ የስንዴ ሞዛይክ ቫይረስ (ደብሊው ኤስ ኤም ቪ) ናቸው፡፡ ሁለቱም ዓይነት የቫይረስ በሽታዎች ስንዴን፣ ተመሳሳይ የሆኑ የሳር ዝርያ ያላቸውን የብርዕና ሌሎች ሰብልችን ሊያጠቁ ይችላሉ፡፡ እንደ እድል ሆኖ ግን እንኚህ በሽታዎች በሃገራችን ታዋቂ አይደሉም፡፡