ድህረ ምርት አያያዝ


 አጨዳና ውቂያ

ስንዴ በደንብ ከደረሰ በኋላ ቀለሙ ወደ ቢጫነት በተለወጠ ከ10 – 15 ቀን ጠብቆ የድርቀት መጠኑን በማየት ማጨድ በማሳ ላይ በመራገፍ የሚደርሰውን ብክነት ለማስቀረት ይረዳል፡፡ መታጨድ ያለበት የዘር ርጥበት ይዘቱ ከ16-18 በመቶ ሲሆን ነው፡፡ በተለምዶ ስንዴ የሚታጨደው በሰው ኃይል ሲሆን የሚወቃው ደግሞ እንሰሳትን በመጠቀም በአውድማ ላይ ነው፡፡ ነገር ግን በዘመናዊ ኮምባይን ወይም መሣሪያው በቆመበት ሞተር የተገጠመለት መውቂያ መጠቀም ይቻላል ፡፡

በአሁኑ ጊዜ ውጤታማ የሆኑ የተለያዩ የመውቂያ መሳሪያዎች በገበያ ላይ አሉ፡፡ የክልል ግብርና ቢሮዎች ከነዚህ ውሰጥ ተስማሚ የሆኑትን መውቂያዎች በመለየት ስንዴ አብቃይ በሆኑ አካባቢዎች በአርሶ አደር ማሰልጠኛ ማዕከላት ሰርቶ በማሳየት አርሶ አደሩን ማስተዋወቅ አለባቸው፡፡ መውቂያ መሳሪያዎችን መጠቀም በውቂያ ጊዜ በመሰባበርና በመፈንከት የሚባክነውን ምርት ለመቀነስ ይረዳል፡፡

ክምችትና ነቀዝን መከላከል

ስንዴ በጎተራ ውስጥ በተለያዩ ተባዮች ይጠቃል፡፡ ስንዴን በአግባቡ አድርቆ በ12.5 በመቶ የርጥበት ይዘት መከማቸት አለበት፡፡ ጎተራው (ማከመቻው) አይጥና ወፍ የማያስገባና ከነቀዝ ነፃ መሆን አለበት፡፡ ከተቻለም ንፁህ ጆንያ መጠቀም በጥሩ ሁኔታ ለማከማቸት ይረዳል፡፡ ስንዴው የሚከማቸው ከሦሰት ወር በላይ ከሆነ በአክትሊክ ሱፐር ወይም ማላታይን 5 በመቶ (ማላታይን 5 በመቶ) ዱቄት በማከም ከርጥበት ነፃ [48] በሆነ ቦታ መከማቸት አለበት፡፡ ሜታል ሳይሎና ተባይ የማያስገባ ጆንያ ስንዴን ለማከማቸት መጠቀም ይመከራል፡፡

ስንዴን በክምችት ወቅት ከሚያጠቁት ተባዮች ዋነኛው የስንዴ ነቀዝ ነው፡፡ ነቀዝ ስንዴን በተከማቸበት በማጥቃት ምርቱንና ጥራቱን ይቀንሳል፡፡ በየጊዜው በመከታተል መቆጣጠር ሲቻል ይኸውም ንጹህና ቀዜቃዛ ቦታ ላይ ጎተራውን ማስቀመጥና እንደ አክተሊክ 2 በመቶ ደስት ባሉና በመሳሰሉት ፀረ-ተባይ ኬሚካሎች በማከም መከላከል ይቻላል፡፡