የሰብል ፈረቃ ማለት ቁጥራቸው ሁለትና ከዚያ በላይ የሆኑ ሰብሎችን ትክክለኛ እቅድ በተከተለ መንገድ በአንድ የተወሰነ መሬት ላይ አፈራርቆ ማምረት ነው፡፡ ለስንዴ ምርት መቀነስ አንዱ ዓይነተኛ ምክንያት በአንድ ማሳ ላይ ስንዴንና የብርዕ ሰብልችን ከዓመት ዓመት አከታትሎ በመዝራት ነው፡፡ ሰብልን ማፈራረቅ የአፈርን ለምነት ከመጠበቅ በተጨማሪ የቀጣዩን ሰብል (የስንዴ) ምርታማነትን ያሻሽላል፡፡ የአረም ጥቃት፣ ተባዮችና አፈር ወለድ በሽታዎች ሰብልን በማፈራረቅ ሊቀንሱ ይችላሉ፡፡ ስንዴ ናይትሮጅንን ከአየር የሚሰበስቡ ሰብልችን (ጥራጥሬ ሰብልችን) አስከትሎ በመዝራት የሚጨመረው የዩሪያ መጠን እንዲቀንስ ይረዳል፡፡ ስለዚህ ሰብልን ለማፈራረቅ ሲታቀድ ይህንን ውጤት ሊያስገኝ በሚያስችል መልኩ ታስቦ መቀናጀት ይኖርበታል፡፡ ከስንዴ በኋላ ስንዴን ከመዝራት ጥራጥሬዎችን እንደ ባቄላ፣ አተርንና ሽምብራ፣ ተልባ፣ ጎመን ዘር፣ ኑግ፣ ቅመማቅመምና የመሳሰለትን ሰብሎች አስከትሎ ስንዴን መዝራት ከፍተኛ የስንዴ ምርትና ገለባን ያስገኛል፡፡ ስለዚህ የምርምር ውጤቶች እንደሚጠቁሙት ባቄላና ጎመን ዘርን ተከትሎ ስንዴ ቢዘራ በሄክታር ከ6 እስከ 13 ኩንታል ተጨማሪ ምርት እንደሚገኝ ተረጋግጧል፡፡:: ስለዚህ ስንዴን ከእነዚህ ሰብሎች ጋር በማደራረቅ ዘላቂ ምርታማነትን ማረጋገጥ ይቻላል፡፡
በኮትቻ አፈር ላይ ቀድሞ በተዘራ ስንዴ ማሳ ላይ ስንዴው ከታጨደ በኋላ እንደ ጓያ፣ ምስር፣ አብሽና ሽምብራ መዝራት ይቻላል፡፡ ይህም በዓመት ሁለት ጊዜ በማምረት የአርሶ አደሩን ገቢ ከማሳደጉም በላይ በተጓዳኝ የአፈርን ለምነት ጠብቆ ለማቆየት ይረዳል፡፡