በዝናብ የሚለማ ስንዴ የዘር ጊዜ የሚወሰነው የክረምቱ ዝናብ በአስተማማኝ ሁኔታ መግባቱ ሲረጋገጥ ነው፡፡ ዋናው የክረምት ዝናብ መግቢያው አካባቢ (እንደአካባቢው ሁኔታ ከግንቦት መጨረሻ እስከ ሰኔ መጀመሪያ) የሚጥለው ዝናብ በማሳው ውስጥ ያሉትን አረሞች እንዲበቅሉ ስለሚያደርጋቸው አርሶ አደሮች ይህንን አጋጣሚ በመጠቀም የእርሻ ስራቸውን የሚጀምሩ ሲሆን በዚህም የእርሻ ስራ እንቅስቃሴ ቀድመው የበቀሉትን አረሞች ከማሳቸው ያስወግዳሉ፡፡
የስንዴ የዘር ወቅት እንደ ዝናቡ አመጣጥ እና የአፈር ዓይነት ከሰኔ ወር አጋማሽ እስከ ሐምሌ መጀመሪያ ሲሆን ምርት ለመጨመር የዝናብ እጥረት ባለባቸው አካባቢዎች ሳይቀር ዝናብ እንደጀመረ ቀድሞ መዝራት ይመከራል፡፡ ይህም በተደጋጋሚ በሰብል መድረሻ ጊዜ የሚከሰተውን የዝናብ እጥረትን ማምለጥ ያስችላል፡፡ በኮትቻ አፈር ላይ የንሽ ጊዜን በመጠቀም ቀድሞ መዝራት ይመከራል ምክንያቱም በአንድ የምርት ዘመን ሁለት ጊዜ እንዲመረት ያስችላል፡፡
ጥሩ የሰብል ብቅለት ለማግኘት ዝናቡ መዝነብ ከጀመረና በአፈር ውስጥ የእርጥበት ክምችቱ እስከ 20 ሚ/ሜ ሲደርስ ዘር መዘራት እንደሚገባው ለአምራች አርሶ አደሮች ተገቢው የኤክስቴንሽን የምክር አገልግሎት መሰጠት አለበት፡፡
ዘግይቶ ከተዘራ ዝናብ ቀድሞ ሊያቋርጥ ስለሚችል ፍሬ በደንብ ሳይሞላ ስለሚቀር የምርት ቅነሳ ሊያስከትል ይችላል፡፡ ፍሬው በደንብ ያልሞላ የስንዴ ምርት ዱቄቱ በሚፈጭበት ሰዓት ከደረጃው 75% በታች ስለሚሆንና በዚህም ምክንያት የዱቄት ፋብሪካዎች ምርቱን ላልመግዛት ያንገራግራሉ፡፡